ነሐሴ 05 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ሀገራቸው የፍልስጤምን መንግስት እውቅና እንደምትሰጥ አስታወቁ። ይህ ውሳኔ በመጪው መስከረም ወር በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በይፋ ይፀድቃል ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ እርምጃ በካቢኔያቸው እና በበርካታ የአውስትራሊያ ዜጎች ግፊት መደረጉን ገልጸው፣ ለጋዛ ህዝብ የሚደርሰውን ስቃይ እና ረሃብ አስመልክቶ ከመንግስት ባለስልጣናት የሚሰነዘረውን ትችት ተከትሎ ነው ብለዋል። የእስራኤል እና የፍልስጤም መንግስታት ቋሚ እስካልሆኑ ድረስ ሰላም ጊዜያዊ ብቻ ሊሆን ይችላል ያሉት አልባኔዝ፣ አውስትራሊያ የፍልስጤም ህዝብ የራሳቸው መንግስት የማግኘት መብታቸውን ትገነዘባለች ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስትራሊያ የፍልስጤምን መንግስት እውቅና የምትሰጠው ፍልስጤም ከሰጠችው ቁርጠኝነት በመነሳት እንደሆነም ገልጸዋል። ከእነዚህ ቁርጠኝነቶች መካከል ጋዛን ከወታደራዊ ነፃ ማድረግ፣ ምርጫ ማካሄድ እና ሃማስ በፍልስጤም መንግስት ውስጥ ቦታ እንዳይኖረው ማድረግን ያጠቃልላል ተብሏል።
ይህ የአውስትራሊያ ውሳኔ የእስራኤልን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የቅርብ ጊዜ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የመጣ ሲሆን፣ ኔታንያሁ በአውስትራሊያ እና የፍልስጤም መንግስት እውቅና ለመስጠት በሚንቀሳቀሱ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ላይ ትችት መስንዘራቸው ይታወሳል።
አውስትራሊያ ይህንን እርምጃ ለመውሰድ ማቀዷ፣ ከፈረንሳይ፣ ከብሪታንያ እና ከካናዳ ጋር በመሆን የፍልስጤምን መንግስት እውቅና ለመስጠት በዝግጅት ላይ ካሉት ሀገራት ጋር እንደምትቀላቀል ያመለክታል።
ምላሽ ይስጡ