ነሐሴ 05 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ግንባታው የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር በይፋ እንደሚመረቅ ከተገለጸ ወዲህ ግብጽ የምረቃ ስነ-ስርዓቱ እንዲስተጓገል እየሰራች መሆኑን ባለሙያዎች ለመናኸሪያ ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የአባይ ወንዝ እና የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ለአገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሙያዊ ማብራሪያ በመስጠትና የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በመሟገት የሚታወቁት አቶ ሙሳ ሼኮ ባለፈው ሳምንት ኳታር በሚገኘው የአልጄዚራ ዋና ስቲዲዮ “ለመረዳት መሞከር” በተሰኘ የውይይት መድረክ ላይ ከግብጽ ብሄራዊ ደንህነትና መረጃ መስሪያ ቤት አማካሪ እና ከሱዳኑ ተወካይ ጋር በመሟገት የኢትዮጵያን እውነታ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡
ግብጽ ባለፉት 14 አመታት ስታደርግ የነበረውን የማወናበድና የማደናገር ስልት ተወካዩም ይዘው እንደቀረቡ በማመላከት፤ ሱዳንን በመወከል በውይይቱ የተሳተፉት ባለሙያም የጠራ ሃሳብ አለመያዝና የማወናበድ አካሄድ የመከተል ዝንባሌ እንደነበራቸው አስረድተዋል፡፡
ባለሙያው አሁንም ቢሆን ግብጽ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የምርቃት ስነ-ስርዓትን ለማደናቀፍ የቻለችውን ሁሉ እያደረገች መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡ ተጠናቋል ብሎ ጉዳዩን ችላ ማለት እንደማይገባው አመላክተዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪና በመካከለኛው ምስራቅ ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው አሁንም ቢሆን ምንም አይነት ክፍተት መፍጠር እንደማይገባ አፅኖት ሰጥተዋል፡፡ በተለይም ውስጣዊ አንድነት እና የጸጥታ ችግር ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ በመጠቆም፣ የግብጽን ጉዳይ በሁለት ከፍሎ መመልከት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ይህም አሁን ባለውም ይሁን ባለፉት መንግስታት ኢትዮጵያ እና የአባይ ወንዝ ጉዳይን የሥልጣን ማራዘሚያ አድርጎ መመልከት ቀዳሚው ሲሆን በህዝቡ በኩል ደግሞ በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ዘመቻ ማካሄድና ኢትዮጵያ ከአለም እንድትገለለ ማድረግ ተጠቃሽ ተግባራቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለአብነት ግብፆች በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሃንን በመቆጣጠር ኢትዮጵያ ላይ የሚዲያ ዘመቻ እያደረጉ እንዳሉና ባለፉት 12 ዓመታት በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከኢራቅና አፍጋኒስታን በበለጠ ሽፋን እንዲገኝና ትኩረት እንዲስብ ማድረጋቸውን በማስረዳት፣ በሀገሪቱም ቢሆን ከ4 ሺህ በላይ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የመቀስቀስ ስራዎች እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከሰሞኑን በሰጠው መግለጫ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ስራ ከገቡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ተርባይኖች 4ሺህ 300 ያህል ሜጋ ዋት ኃይል እንዳገኘና አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁ ይታወቃል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ