ነሐሴ 05 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአፍሪካ ልማት ባንክ (AfDB) እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን በቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ፋይናንስ ለማሰባሰብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል። በውሉ መሰረት ባንኩ የ6.2 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ መሠረተ ልማትን ለመገንባት የሚያስፈልገውን የገንዘብ ምንጭ የማሰባሰብ ሥራውን ይመራል ተብሏል።
ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ሲጠናቀቅ የአፍሪካ ትልቁ አውሮፕላን ማረፊያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በአቡሰራ ይገነባል ተብሏል። ስራ ሲጀምርም በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል ተብሏል። ሙሉ አቅሙ ሲጠናቀቅ ደግሞ እስከ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ ያስችላል የተባለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ ከፍተኛ ተጓዥ ያላቸው የአውሮፕላን ማረፊያዎች በዓመት ከ18 እስከ 29 ሚሊዮን መንገደኞችን ያገለግላሉ ተብሏል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ የቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክትን ፋይናንስ የማሰባሰብ ኃላፊነት የተሰጠው ባንኩ በአፍሪካ ውስጥ ባለው ስልታዊ መሠረተ ልማት ግንባታ እና ውስብስብ ስምምነቶችን በማዘጋጀት ባለው የረጅም ጊዜ ልምድ የተነሳ ነው ተብሏል። ባንኩ የመንግስትን እና የግሉን ዘርፍ የገንዘብ ድጋፍን በማስተባበር የአፍሪካን የልማት ቅድሚያዎች ለመደገፍ የሚያስችል ልዩ ብቃት አለው ተብሎለታል።
አፍሪካ ውስጥ ትልቁ እና ስኬታማው የአየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቡድን ይህንን አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ የራሱ የሆነውን የ2035 የዕድገት ስትራቴጂ ቁልፍ ምሰሶ አድርጎ ይመለከተዋል ነው የተባለው። ፕሮጀክቱ የአውታረ መረብ ማስፋፋትን፣ የመሠረተ ልማትን እና የሰው ኃይል ኢንቨስትመንትን በማጎልበት የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ታሳቢ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
ምላሽ ይስጡ