👉በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሰደዳቸውም ተመላክቷል
ነሐሴ 05 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ስፔን ውስጥ ከ39,000 ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት በሰደድ እሳት መቃጠሉን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ። ከፍተኛ ሙቀትና ድርቅ በብዙ አካባቢዎች የእሳት አደጋ እንዲከሰት በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲሰደዱ ተገደዋል ነው የተባለው።
በተለይ በጋሊሺያ፣ ካስቲላ እና ሊዮን፣ እንዲሁም በናቫራ ግዛቶች ውስጥ በርካታ የእሳት አደጋዎች አሁንም በከፍተኛ ፍጥነት እየነደዱ ነው ተብሏል። የእሳት አደጋው የተከሰተው በቅርብ ጊዜ በስፔን ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ የሙቀት መጠን እና በከባድ ድርቅ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡
የስፔን የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ከፖርቹጋል ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ የተቀሰቀሰው የእሳት አደጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም በመስፋፋት ላይ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን ሁኔታውን ለመቆጣጠር በመቶዎች የሚቆጠሩ የእሳት አደጋ ተከላካዮች በምድር ላይ እንዲሁም በአውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች አማካኝነት በአየር ላይ እየተንቀሳቀሱ ነው ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረትም የሰደድ እሳቱን ለመዋጋት ስፔንን ለመርዳት አቅዷል የተባለ ሲሆን የሙቀት መጠኑ እና ድርቁ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊሻሻል የሚችልበት ሁኔታ ስለሌለ፣ የእሳት አደጋው ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተሰግቷል።
ምላሽ ይስጡ