ነሐሴ 05 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በተለያዩ አካባቢዎች ከክረምት ወር መግቢያ ጀምሮ የዝናብ ስርጭት ቢኖርም በሰሜን ወሎ ዞን ቆላማ አካባቢዎች ላይ እጥረት አጋጥሞ እንደነበረ እና በግብርና ስራ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን የዞኑ ግብርና ቢሮ ለጣቢያችን መግለፁ ይታወሳል፡፡
አሁን ላይ የዝናብ ስርጭቱ አጥጋቢ የሚባል ባይሆንም አርሶ አደሩ ዘር መዝራት የሚያስችለውን ያህል ዝናብ መጣል መጀመሩን የዞኑ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ተገኘ አባተ ገልፀዋል፡፡
በዞኑ ከ231 ሺህ ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት መኖሩን እና ወደ 40 በመቶ ያህሉን የሚሸፍኑ ቆላማ አከባቢዎች የዝናብ እጥረት አጋጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ዝናብ መጣል መጀመሩን ተከትሎ አርሶ አደሮች ዘር መዝራት መጀመራቸውን በመግለፅ፣ ነገር ግን የትንበያው መረጃ ከባድ ዝናብ እንደሚኖር የሚያሳይ ቢሆንም አሁንም ከመደበኛ በታች እየጣለ መሆኑን፤ በዚሁ ከቀጠለ ሰብሉ ሲደርስም ተገቢውን እርጥበት ባለማግኘት ለብልሽት ሊጋለጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ማዳበሪ እንዲያገኝ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ እና እስካሁን በቂ አቅርቦት መኖሩን በመጥቀስ በዚህ የክረምት ወራት ለማሰራጨት የታቀደው 217 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ መሆኑን እና እስካሁን 170 ሺህ ኩንታል ማሰራጨት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ የጀመረውን የዝናብ ስርጭት በመጠቀም በአጭር ግዜ የሚደርሱ ዘሮችን አርሶ አደሩ እንዲዘራ የግብርና ባለሙያዎች ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ሃላፊው ገልፀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ