ነሐሴ 01 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በስዊድን የደም ለጋሾች የሚያገኙት ምስጋና ደም በሰጡበት ወቅት ብቻ የተገደበ አይደለም ። የሰጡት ደም አንድን ታካሚ ህይወት ለመታደግ ሲውል፣ የደም ልገሳ ማዕከላት ለለጋሾቹ የጽሑፍ መልዕክት በመላክ ያደረጉትን በጎነት በግልጽ ይነግሯቸዋል ነው የተባለው።
ይህ ልዩ አሰራር የደም ልገሳን ከመደበኛ ልማድነት ወደ ህይወት አድን ተልዕኮ ከፍ አድርጎታል ነው የተባለው።
አሰራሩ የሚጀምረው ደም ከተሰጠ በኋላ ነው የተባለ ሲሆን ደሙ የህክምና ምርመራዎችን አልፎ ለአገልግሎት ዝግጁ ሲሆን ለጋሹ የመጀመሪያውን መልዕክት ይቀበላል ተብሏል።
ከሁሉም በላይ ግን፣ ደሙ በእርግጥ ለታካሚው ሲሰጥ ለጋሹ “ደምዎ የሰውን ህይወት አድኗል” የሚል ሌላ የጽሑፍ መልዕክት ይላክለታል ነው የተባለው።
የዚህ አሰራር ዋና ዓላማዎች በዋናነት ሦስት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን የመጀመሪያው፣ ደም የለገሰውን ሰው በቀጥታ ማመስገን እና የጥረቱን ፍሬ እንዲያይ ማድረግ መሆኑ ተመላክቷል። ይህ ደግሞ በድጋሚ ደም ለመስጠት ከፍተኛ ተነሳሽነት ይፈጥራል ተብሏል።
ሁለተኛው፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት ሲሆን፣ ሰዎች የደም ልገሳ የሌላን ሰው ህይወት የመታደግ እውነተኛ መንገድ መሆኑን እንዲገነዘቡ ያደርጋል ተብሏል።
በመጨረሻም፣ ይህ ዘዴ የደም ባንኮች በቂ የደም ክምችት እንዲኖራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው የተባለው።
ስዊድን የጀመረችው ይህ አዎንታዊ ተሞክሮ በአሁኑ ወቅት እንደ ብሪታንያ እና ሌሎች ሀገራት በደም ልገሳ ማዕከሎቻቸው ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል ነው የተባለው።
ይህ አሰራር የደም ልገሳ ሂደት ላይ ግልጽነትን በማምጣት እና ለጋሾችን በማበረታታት የጤና ስርዓቱን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ