ሐምሌ 29 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኢትዮጵያ ሐገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል የሚካሄደውን የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የምክክር ሂደት እንዳያከናውን እንቅፋት ለመሆን የሚሰሩ አካላት አሁንም እኩይ ተግባራቸውን የቀጠሉ ቢሆንም የክልሉ ህዝብ ጦርነትን እምቢ እንዲልና ከሰላም ፈላጊው ጎን እንዲቆም የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ፓርቲ አሳሰበ፡፡
በተለይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘው የህወሃት ቡድን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በክልሉ አጀንዳ ለማሰባሰብ እና ምክክር ለማድረግ የጀመረውን ጥረት ለማደናቀፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ሲሉ፤ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ስምረት ፓርቲ ኮሚኒዩኬሽንና ሚዲያ ዘርፍ ምክትል አስተባባሪ አቶ ጣዕመ አረዶም ከጣቢያችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡
ከፖለቲካዊ መፍትሄዎች ባሻገር የፌዴራል መንግስቱ የኃይማኖት አባቶችን እና የሀገር ሽማግሌዎችን በመላክ ቡድኑን ለማናገርና ሰላም እንዲወርድ በተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንዲሁም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ ለማሰባሰብ እና የምክክር ሂደቱ በክልሉ እንዲጀመር ለማድረግ እየጣረ ቢሆንም ቡድኑ ከሰላማዊ ምክክር ይልቅ ለጦርነት የሚያርገውን ዝግጅት አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በክልሉ አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ በቀላሉ ይሳካል ተብሎ ባይገመትም፤ የክልሉ ህዝብ ሰላም ከሚፈልገው አካል ጎን መቆም እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ቡድኑ አሁንም ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር ጭምር ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው ያሉት አቶ ጣዕመ፤ የትግራይ ህዝብ ጦርነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ካለፈው ታሪክ በመማር ጦርነትን በቃኝ ማለት እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ