ሐምሌ 29 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በቂ የብድር አገልግሎት ባለማግኘታቸው እምብዛም ምርታማ ያለመሆን እና ዘርፉም ያለመዘመን ችግር እንደሚስተዋልበት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የግብርና ሚኒስቴር ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመሆን የግብርና ፋይናንስ ትግበራ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ለጣቢያችን አስተያየት የሰጡት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አርሶ አደሩ በቂ የብደር አገልግሎት ማግኘት ከቻለ የማምረት አቅሙን የማሳደግ አለፍ ሲልም ዘመናዊ መሳሪያዎችን ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ባለው አሰራር አርሶ አደሩ ያለማስያዣ የብድር አቅርቦት የሚያገኝበት አግባብ ባለመኖሩ በሚፈለገው ልክ ዘርፉ እንዳያድግ አድርጎት መቆየቱን እና አርሶ አደሩም የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ሳይሆን መቅረቱን የሚያነሱት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ሞላ አለማየሁ ናቸው፡፡
ዘርፉን ለማሳደግ እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲቻል ይህ አሰራር ሊተገበር ይገባል ብለዋል።
ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክሩት ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶ/ር ተስፋ ነጋ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ከተመቻቸ ከአርሶ አደሮቹ ባለፈ ሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችላት አንስተዋል፡፡
ነገር ግን ያለምንም ማስያዣ ብድር ሲሰጥ ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችል በመሆኑ ኪሳራ እንዳያጋጥም ለተገቢው አላማ መዋሉ ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ዘርፉ ሰፊ በመሆኑ የብድር አቅርቦቱ ሲመቻች የተሻለ ምርታማ እንዲሆኑ የሚረዳ በመሆኑ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በስፋት እንዲመረቱ ያደርጋልም ብለዋል።
የሀገሪቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚ ከግብርናው ዘርፍ የሚመነጭ በመሆኑ ለዘርፉ ትኩረት መስጠት ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት መጠን ማደግ ዋስትና ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ሃሳባቸውን አሳፍረዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ