ሐምሌ 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በ2017 በጀት አመት በዶሮና እንቁላል ምርት ላይ ለተስተዋለው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የውጭ ምንዛሬ መጨመር የራሱን አስተዋፆኦ ማበርከቱን የኢትዮጵያ ዶሮ አልሚዎችና አቀናባሪዎች ማህበር ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ለዶሮ መኖነት የሚያገለግሉ ሚኒራሎችና ቫይታሚኖቹ ከውጭ ሃገራት የሚገዙ በመሆኑ፤ አሁን ላይ ላለው የዶሮና የእንቁላል ዋጋ መጨመር የውጭ ምንዘሬ ዋጋ መጨመርም ተፅዕኖ ማሳደሩን የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪጅ አቶ ዝናው ፀሃይነህ ተናግረዋል፡፡
ለዶሮ ምርታማነት 80 በመቶውን ድርሻ የሚዘው መኖ መሆኑን የሚያነሱት ሥራ አስኪጁ፤ በቆሎና አኩሪ አተር ለመኖ ዝግጅት የሚያገለግሉ ቢሆንም አኩሪ አተር ለውጭ ገበያ እየቀረበ በመሆኑ በሃገር ውስጥ ያለው አቅርቦት እንዲቀንስ እንዳደገረው ገልጸዋል።
አሁን ላይ መንግስት በመኖ ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉ ሌላኛው ለዋጋው መጨመር ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት አመታት በነበረው የዋጋ አለመረጋጋት ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ አምራቾች ከማህበሩ መውጣታቸውን የገለጹት አቶ ዝናው፤ አሁን ላይ 160 አምራቾች መኖራቸውን ጠቁመው፤ አርቢዎችም ወደ ማህበሩ እየተመለሱ ስለሆነ የዋጋ መረጋጋት ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት ዘርፉ መልሶ እንዲያንሰራራ የግብር ቅነሳ፣ የብድር የእፎይታ ጊዜ ማራዘም፣ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦትና መሰል የፋይናንስ ድጋፎችን እንዲያደርግ ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ