ሐምሌ 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ ምክንያቶች ተገፋፍተው ወደ ጦርነት እንዳይገቡ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን ስምረት ዴሞክራሲያዊ ትግራይ ፓርቲ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
ፓርቲው የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲከበር እየሰራ መሆኑን የስምረት ፓርቲ የኮምዩኒኬሽን ሚዲያ ምክትል አስተባባሪ አቶ ጣእመ አረዶም ተናግረዋል።
አቶ ጣእመ በትግራይ የሚገኙ የጸጥታ ሀይሎች የሰላም ሃይል ወደሚባለው እንዲቀላቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ፓርቲው ለሰላም እየሰራ መሆኑን እና በክልሉ የሚገኙ የፓርቲው አባላትም የአከባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ችግሮች ቢታዩም ችግሩን በሂደት አስተካክሎ መቀጠል እንጂ ወደ ግጭት መግባት ተገቢ አለመሆኑን ጨምረው ገልጸዋል።
በክልሉ ሰላም ተረጋግጦ እና ማህበረሰቡ ከስጋት ነጻ ሆኖ እንዲኖር ማድረግ ይገባል የሚሉት አቶ ጣእመ በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ሀይልም በዚሁ ላይ መስራት ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል።
በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የፌደራል መንግስትን ጨምሮ ሌሎችም አካላት የተለያዩ ጥረቶች እያደረጉ መሆናቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ