ሐምሌ 25 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በሩሲያ ካምቻትካ ባሕረ ገብ መሬት ላይ የሚገኘው በአውሮፓና እስያ ውስጥ ረጅሙና ንቁ እሳተ ገሞራ የሆነው የክሉቼቭስኮይ ተራራ፣ ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ሱናሚ ከተከሰተ ከሰዓታት በኋላ ረቡዕ ዕለት ፈንድቷል ተብሏል።
8.8 መጠን ያለው የመሬት ውስጥ መንቀጥቀጥ የሩሲያን ምስራቃዊ የባሕር ዳርቻ በ13 ጫማ ከፍታ በሱናሚ ካጥለቀለቀ በኋላ፣ እሳተ ገሞራው በምዕራባዊ ተዳፋት ላይ በሚያብረቀርቅ ላቫ እና ፍንዳታ መውረድ ጀምሯል ሲል የሩሲያ የሳይንስ አካዳሚ አረጋግጧል።
አስደንጋጩ ክስተት ቢኖርም፣ የሩሲያ የቱሪስት መስህብ ስፍራ በመሆኑ በርካታ ጎብኚዎች ጉዟቸውን እንዳልሰረዙና ይህን ልዩ ክስተት ለመመልከት ጉጉት እንዳላቸው ተገልጿል።
ይህ እሳተ ገሞራ ከዋና ከተማዋ ፔትሮፓቭሎቭስክ-ካምቻትስኪ በ450 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ባለፉት ዓመታትም በተደጋጋሚ ጊዜያት ፈንድቷል ተብሏል። ከመሬት መንቀጥቀጡም ሆነ ከሱናሚው የተረጋገጠ የሞት አደጋ አለመኖሩ ታውቋል።
ምላሽ ይስጡ