ሐምሌ 24 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ካናዳ በመስከረም ወር የፍልስጤምን መንግስት በይፋ እውቅና እንደምትሰጥ ማስታወቋን ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ አስታወቁ። ካናዳ በዚህ እርምጃ ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ ጋር ተመሳሳይ አቋም የወሰደች ሲሆን፣ ውሳኔው ግን የፍልስጤም አስተዳደር በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ ለማካሄድ በሚሰጠው ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን ገልጻለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በሰጡት መግለጫ፣ ካናዳ የሁለት መንግስታት መፍትሄን (two-state solution) የምትደግፍ ሲሆን፣ ለዚህም አስተዋፅኦ ለማድረግ የፍልስጤምን መንግስት እውቅና መስጠት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ፣ ይህ ዕውቅና የፍልስጤም አስተዳደር ህዝባዊ ምርጫዎችን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለማካሄድ ግልፅ እና የማይቀለበስ ቁርጠኝነት ሲያሳይ ብቻ ተግባራዊ እንደሚሆን አፅንኦት ሰጥተዋል።
ይህ የካናዳ ውሳኔ ከፈረንሳይ እና ከእንግሊዝ ቀደም ሲል ከነበራቸው ተመሳሳይ አቋም ጋር የሚስማማ ነው ተብሏል። በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በተለይም ስፔን፣ አየርላንድ እና ኖርዌይ የፍልስጤምን መንግስት በቅርቡ እውቅና ከሰጡ በኋላ፣ በሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ ዓለም አቀፍ ግፊት እየጨመረ ነው ተብሏል።
የካናዳ የዚህ ውሳኔ በሰፊው የመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ሂደት ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተመላክቷል።
ይህ የካናዳ የውጭ ፖሊሲ ለውጥ፣ በእስራኤል በኩል ተቃውሞ ሲገጥመው፣ በፍልስጤማውያን እና በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ባሉ የሰላም ደጋፊዎች ዘንድ ደግሞ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኝ እየተነገረ ነው፡፡
ካናዳ የፍልስጤምን መንግስት እውቅና ለመስጠት መወሰኗ፣ በክልሉ ያለውን የሰላም ሂደት ለማነቃቃት እና የፍልስጤም ህዝብ የመንግስትነት ጥያቄን ለመደገፍ እንደ አንድ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ እንደሚታይ የተመላከተ ሲሆን የውሳኔው ተግባራዊነት ግን በፍልስጤም የውስጥ የፖለቲካ ሂደት ላይ የተመሰረተ ይሆናል ተብሏል፡፡
ምላሽ ይስጡ