ሐምሌ 23 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ዮርዳኖስ ዓለምሰገድ፣ ሄዋን ግደይ እና እስከዳር ወሰን የተባሉ ተጠርጣሪዎች የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ 93 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን ግለሰቦቹ በእጃችን ላይ የተለያዩ የውጭ ሀገር ገንዘቦች የሚገኙ በመሆኑ የምንዛሬ አገልግሎት እንሰጣለን በሚል በርካታ ግለሰቦችን የማሳመንና ለህገ ወጥ ተግባራቸው ተባባሪ የማድረግ እንቅስቃሴን አድርገዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሌላም ጊዜ እንደሚያደርጉት ይህንን ምንዛሬ የሚፈፀሙ ግለሰቦችን በማፈላለግ ላይ ሳሉ በሁኔታቸው ጥርጣሬ ውስጥ የገቡ መረጃ ሰጪዎች ለፖሊስ ጥቆማ አድርገዋል፡፡ የቡልቡላ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያም የደረሰውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ባደረገው ክትትል ሦስቱንም ተጠርጣሪዎች ከነ ኤግዚቢታቸው በቁጥጥር ስር ሊያውላቸው ችሏል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅትም ሀሰተኛ ሰባት መቶ የአሜሪካ ዶላርና ሦስት ሺህ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ድርሀም የተያዘ ሲሆን በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ወንጀል ተፈጽሞብኛል የሚል አካል ቡልቡላ ፖሊስ ጣቢያ በመቅረብ መረጃ መስጠት የሚችል መሆኑንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ዜጎች የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን በባንኮችና ለዚሁ ተግባር መንግስት ፈቃድ በሠጣቸው ተቋማት ምንዛሬ አለመፈጸማቸው ህገ ወጥ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር የሀገርን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ ሊጎዳ የሚችል ተግባር መሆኑ ይታወቃል፤ በመሆኑም ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል እንቅስቃሴዎችን ሲያይ ለፖሊስ መረጃ በመስጠት የተለመደውን ትብብሩን እንዲያደርግም የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ምላሽ ይስጡ