ሐምሌ 22 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ኃያል እህት ኪም ዮ ጆንግ፣ ከአሜሪካ ጋር በኑክሌር ትጥቅ ማስፈታት (denuclearization) ዙሪያ ምንም ዓይነት ንግግር እንደማይኖር አስታውቀዋል። ይህ መግለጫ በአሜሪካ እና በሰሜን ኮሪያ መካከል በተቋረጡት የኒውክሌር ድርድሮች ላይ ተጨማሪ ማነቆ እንደሚሆን ይጠበቃል ተብሏል።
ኪም ዮ ጆንግ በሰጡት መግለጫ፣ የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ሁኔታ የማያሻክር እውነታ መሆኑን እና ትጥቅ የማስፈታት ጥያቄዎችን መሰረት ያደረገ ማንኛውም አይነት ንግግር “ከንቱ” እና “የጊዜ ብክነት” መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የሚያሳየው፣ ሰሜን ኮሪያ የራሷን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት እውቅና እንድታገኝ ያላትን የቀደመ አቋም አሁንም አጥብቃ እንደያዘች ነው ተብሏል፡፡
ይህ አቋም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚቀርበውን የኑክሌር ትጥቅ ማስፈታት ጥሪ በግልጽ የሚቃረን ነው የተባለ ሲሆን፤ የሰሜን ኮሪያ አገዛዝ የኒውክሌር መርሃግብሮቿን የአገሪቱ የመከላከል አቅም ወሳኝ አካል አድርጎ እንደሚመለከት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል ነው የተባለው።
የኪም ዮ ጆንግ መግለጫ፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ያለውን ውጥረት የበለጠ ሊያባብሰው የሚችል ሲሆን፣ ለወደፊት በሁለቱ አገራት መካከል የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዴት ሊቀጥል እንደሚችል ጥያቄዎችን አስነስቷል።
ዓለም አቀፍ ተንታኞችም የሰሜን ኮሪያን ጽኑ አቋም እና የአሜሪካን ምላሽ በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ