ሐምሌ 22 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ኢትዮጵያ በበሽታው ስርጭት ከአፍሪካ አንደኛ፤ በዓለም ደግሞ ከህንድ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በጥናት መረጋገጡን የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እየተበራከተ ያለው የእብድ ውሻ በሽታ እንደሌሎቹ የማህበረሰብ የጤና ጠንቆች ትኩረት እንዳልተሰጠውና ስርጭቱም እየተስፋፋ መሆኑን በቢሮው የዝግጁነትና የአቅም ግንባታ አስተባባሪ አቶ ደባልቄ አባተ ለጣቢያችን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ባለቤት አልባ ውሾች መበራከታቸውን የተናገሩት አስተባባሪው፤ በዋናነት ጉዳዩ የሚመለከተው የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮምሽን ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት አለመስራቱ ችግሩ እንዲስፋፋ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በዚህም በ2017 በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ 11 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ጥናት ሪፖርት ከተደረገባቸው አከባቢዎች ብቻ ከ2ሺ 700 በላይ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን አቶ ደባልቄ ገልጸዋል፡፡
በክረምት ውሾች ሲርባቸው፣ እንዲሁም የመራቢያ ጊዜያቸው ሲደርስ የበሽታው ስርጭት እንደሚባባስ ገልጸው፣ የ2018 በጀት ዓመት ከገባ በኃላም በዚሁ ምክንያት የ3 ሰዎች ህይወት እንዳለፈ አመላክተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ልማት ኮምሽን በጉዳዩ ዙሪያ ከጤና ተቋማት እና ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ በኮምሽኑ የእንስሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ አቶ የሽዳኛ በላይሁን አስታውቀዋል፡፡
በከተማዋ በየጊዜው የውሾች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የመላከቱት ቡድን መሪው፤ በልማት ምክንያት ሰዎች ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወሩ ውሾች ተነጥለው ስለሚቀሩ ለቁጥጥሩ ተግዳሮት መፈጠሩን አመላክተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር ከሆቴሎችና ተቋማት እንዲሁም ከግለሰቦች የሚጣሉ ተረፈ ምርቶችን የሚመገቡ ባለቤት የሌላቸው ውሾች መበራከታቸው በሽታው እንዲስፋፋ ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚሰራው ስራ ሰፊ ጥናት እንደሚያስፈልገው የገለጹት ባለሙያው፤ በባለድርሻ አካላት በኩል የትኩረት ማነስ፣ የመድሃኒት ዋጋ መወደድ፤ የማህበረሰቡ የግንዛቤ ክፍተት ዋነኛ ተግዳሮት መሆናቸውን በመግለጽ፤ ችግሩ ሳይባባስ በጋራ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ