👉የእርዳታ አቅርቦትም በአየር መጀመሩ ተገልጿል
ሐምሌ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰርጥ ውስጥ በሚገኙ ሦስት የሕዝብ ብዛት ባለባቸው አካባቢዎች ዕለታዊ የ10 ሰዓት “ታክቲካዊ የውጊያ ማቆም” ማድረጉን አስታውቋል። ይህ እርምጃ ሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ ለማመቻቸት ያለመ ሲሆን፣ በአየር ላይ የሚደረግ የእርዳታ ማከፋፈልም ተጀምሯል ነው ተብሏል፡፡
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (IDF) እንዳስታወቀው፣ ይህ የጥቃት ማቆም በጋዛ ከተማ፣ በደይር አል-ባላህ እና በሙዋሲ አካባቢዎች የሚደረግ ሲሆን፣ በየቀኑ በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የሚቆይ ይሆናል ተብሏል። ይህ ውሳኔ በጋዛ ውስጥ እየተባባሰ የመጣውን የረሃብ ስጋት ለመቅረፍ እና እስራኤል በዓለም አቀፍ ደረጃ እየገጠማት ያለውን ትችት ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የእስራኤል ጦር፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች ሰብአዊ ድርጅቶች የምግብ እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለጋዛ ህዝብ እንዲያደርሱ የሚያስችሉ አስተማማኝ መንገዶችን እንደሚያቋቁም አስታውቋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ጎረቤት ዮርዳኖስ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በጋዛ ሰርጥ ላይ በአየር ላይ የእርዳታ ዕቃዎችን ማውረድ ጀምረዋል። ዮርዳኖስ ሶስት የአየር ላይ ማከፋፈያዎችን ማድረጓን የገለጸች ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችም ከእርሷ ጋር በመተባበር 25 ቶን ምግብና አቅርቦቶችን በበርካታ አካባቢዎች አውርደዋል ነው የተባለው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) የእስራኤልን እርምጃ በደስታ የተቀበለ ሲሆን፣ በጋዛ ውስጥ ለሦስት ወራት ያህል የሚበቃ ምግብ መኖሩን ወይም በመንገድ ላይ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ፣ ዕርዳታው ለሁሉም የተቸገሩ ሰዎች መድረሱን ለማረጋገጥ የተኩስ ማቆም እንደሚያስፈልግ አጽንዖት ሰጥቷል።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር ኃላፊ ዶ/ር ሙኒር አል-ቡርሽ፣ የተከሰተውን የህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለማከም ተጨማሪ የህክምና ቁሳቁሶች እና ሌሎች እቃዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ጠይቀዋል።
የተኩስ ማቆሙ የተደረገው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል የነበረው የእርቅ ድርድር በሂደት ላይ ባለበት ወቅት ነው ተብሏል። እስራኤል ሐማስ እጅ ከሰጠ፣ መሳሪያውን ካስረከበ እና ወደ ስደት ከሄደ ጦርነቱን ለማቆም ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፣ ነገር ግን ሐማስ ይህንን ውድቅ አድርጓል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ በጋዛ ውስጥ በረሃብ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የተዘገበ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ህጻናት ናቸው ተብሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ