ሐምሌ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በትላንትናው ዕለት በትግራይ ክልል ደቡብዊ ዞን በምትገኘው መኾኒ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሒዷል።
መናኸሪያ ሬዲዮ ያነጋገራቸው የዲሞክራሲያዊ ጥምረት ትግራይ የኮሙኒኬሽን ኮሚቴ ምክትል አስተባባሪ አቶ ጣዕመ አረዶም ከሰሞኑ እየተካሄዱ ባሉ ሰላማዊ ሰልፎች ዜጎች በጉልበት አንገዛም፤ ተፈናቀዮች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው፤ ከሌሎች ሃይሎች ጋር እየተደረገ ያለው ኢ-ህገመንግስታዊ ግንኙነት መቆም አለበት ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት ህዝቡ ከጦርነት ይልቅ ልማትን አብዝቶ ይሻል ሲሉም ተናግረዋል። ህወኃት ዳግም ወደ ጦርነት ለመግባት የሚያደርገውን ቅስቀሳ ህዝቡ በጽኑ እየተቃወመው መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
አቶ ጣዕመ፣ አሁንም ድረስ ከሌሎች ሀይሎች ጋር እየተደረጉ ባሉ ህገወጥ ግንኙነቶች ዜጎችን የማስፈራራት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸም እና መሰል ችግሮች እየተስተዋሉ ከመሆኑ ባለፈ በክልሉ ከባባድ መሳሪያዎችን የሚታጠቁ ሃይሎች እየታዩ ነው ብለዋል።
በክልሉ ባሉ የፀጥታ አካላት ጭምር ሁኔታውን ለማረጋጋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በማህበረሰቡ በኩል ከሰሞኑ እየተደረጉ ያሉ ሰልፎች ተመሳሳይ ይዘት እንዳላቸው ገልጸው፣ ለችግሩ እልባት ለማግኘት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ቢኖሩም መፍትሄ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡
ህዝቡ ከጦርነት ስጋት መውጣት እንደሚፈልግ በሰላማዊ መልኩ እየገለጸ ቢሆንም፣ ክልሉ ከጦርነት እንዳይላቀቅ የሚፈልጉ አካላት በዝተዋል ሲሉ አቶ ጣዕመ ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው እና ካለፈው ስህተት መማሩን የሚሳዩ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ በክልሉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሃይሎች አካባቢውን ወደ ጦርነት እየገፉ ነው ብለዋል።
ክልሉ በወቅታዊ የጸጥታ ችግር አጣብቂኝ ውስጥ ስለመግባቱ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ