ሐምሌ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ህብረት ለረዥም ጊዜ ሲያስጨንቅ የነበረውን የንግድ ጦርነት ለማስቀረት የሚያስችል ታሪፍ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለፀ። ስምምነቱ አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ምርቶች ወደ አሜሪካ ሲገቡ የ15 በመቶ ታሪፍ እንዲጣልባቸው የሚያስገድድ መሆኑ ተመላክቷል።
ይህ ስምምነት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል እስከ ነሐሴ 1 ድረስ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ 30 በመቶ ታሪፍ እንደሚጣል ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ የተደረሰ ሲሆን፣ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ እፎይታን አስገኝቷል ነው የተባለው።
ስምምነቱ በአብዛኛው በአውሮፓ ከሚገቡ ምርቶች ማለትም እንደ መኪና፣ የኮምፒዩተር ቺፖች እና የመድኃኒት ምርቶች ላይ የሚጣለውን ታሪፍ የሚመለከት ነው የተባለ ሲሆን ምንም እንኳን ይህ ታሪፍ የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ ቀደም ከጠየቀው 20 በመቶ እና ከዛም በላይ ከሆነው 30 በመቶ ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ ከዚህ በፊት ከነበረው አማካይ የታሪፍ መጠን (ከ1 በመቶ አካባቢ) አሁንም ከፍ ያለ መሆኑ ተጠቁሟል።
የጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪኽ ሜትስ ስምምነቱን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን፣ “በአትላንቲክ ማዶ ባለው የንግድ ግንኙነት ላይ አላስፈላጊ ውጥረትን ማስቀረት ችለናል” ብለዋል። ይሁን እንጂ፣ በአትላንቲክ ማዶ ባለው የንግድ ልውውጥ ላይ ተጨማሪ እፎይታ ቢደረግ መልካም ነበር ሲሉም አክለዋል።
ስምምነቱ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሰንት እና በአውሮፓ ህብረት የንግድ ኮሚሽነር ማሮስ ሴፍኮቪች መካከል ከተደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች በኋላ የተገኘ ነው ተብሏል። የአውሮፓ ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎችም ስለ ውይይቶቹ ለኅብረቱ አባል ሀገራት ገለፃ አድርገውላቸዋል ነው የተባለው።
ይህ ስምምነት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በትልቁ የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነታቸው ላይ ውጥረትን ለማርገብ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያሳይ ሲሆን፣ በዓለም ኢኮኖሚ መረጋጋት ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ