ሐምሌ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ በንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፍ የተሰማሩ ፋብሪካዎች አስፈላጊውን የማጠቢያ ማሽን ማሟላታቸውን በማረጋገጥ ፈቃድ እንደተሰጣቸው የኢትዮጵያ ምግብና መድሐኒት ባለስልጣን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አረጋግጧል።
በ20 ሊትር የውሃ ማቅረቢያ ጃር ላይ የሚደረገው ሙሌት በየጊዜው የኬሚካል እጥበት የሚያስፈልገው በመሆኑ፤ በምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ፍቃድ ያገኙ ፋብሪካዎች ለዚያ የሚያገለግሉ ማሽኖችን እንደሚጠቀሙ በባለስልጣኑ የምግብ አምራቾች ተቆጣጣሪ አቶ አዲስ አለቤ ገልጸዋል።
ገና ማምረት ሳይጀመሩ በፊት የማጠቢያ ማሽን ማሟላታቸው ፍቃድ ለማውጣት ዋናው መስፈርት ሆኖ እንደሚቀርብ ያስታወቁት ተቆጣጣሪው፤ በየሶስት ወራት በሚደረግ የቁጥጥር ስራ፣ በማሽን በመታገዝ የተጣራ ውሃ ሙሌት ማከናወናቸውን ተቋሙ እንደሚከታተል ተናግረዋል።
በመዲናዋ አብዛኛው ማህበረሰብ የጃር ውሃ ተጠቃሚ መሆኑን በመረዳት በህገ-ወጥ መንገድ በቤታቸው በማሽን እና ኬሚካል እቃውን ሳያጥቡ ያልተጣራ ውሃ በማከፋፈል ላይ የተሰማሩ መኖራቸውንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ተጠቃሚዎች የጃር ውሃ ሲገዙ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት አርማ ያለበት መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለባቸው የተናገሩት አቶ አዲስ፣ የሚያጠራጥር ነገር ሲያስተውሉ በነጻ የስልክ መስመር 8482 ላይ በመደወል ጥቆማ እንዲሰጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምላሽ ይስጡ