👉ሳውዲ አረቢያ ግን ‘ታሪካዊ ውሳኔ’ ስትል አመሰገነች::
ሐምሌ 18 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)አሜሪካ ፍልስጤምን እንደ መንግስት እውቅና ለመስጠት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ያቀረቡትን እቅድ ‘በፅኑ እንደምትቃወም’ አስታወቀች። በተቃራኒው፣ ሳውዲ አረቢያ የፈረንሳይን ውሳኔ ‘ታሪካዊ’ በማለት አሞካሽታለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የፕሬዝዳንት ማክሮንን ውሳኔ “ግድየለሽነት የሞላበት” ሲሉ ኮንነዋል። ሩቢዮ በትዊተር ገፃቸው ላይ “ዩናይትድ ስቴትስ የኢማኑኤል ማክሮንን የፍልስጤም መንግስት በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እውቅና ለመስጠት ያቀዱትን እቅድ በፅኑ ትቃወማለች ብለዋል።
አክለውም፤ ይህ ግድየለሽነት የሞላበት ውሳኔ የሐማስን ፕሮፓጋንዳ ብቻ የሚያገለግል እና ሰላምን ወደ ኋላ የሚመልስ ነው በማለት በጥቅምት 7 ጥቃት ለደረሰባቸው ሰለባዎች እንደ ፊት በጥፊ መምታት ነው” ሲሉ ጽፈዋል።
በተቃራኒው፣ የሳውዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፈረንሳይን ‘ታሪካዊ ውሳኔ’ በደስታ ተቀብሏል። ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ፣ ሳውዲ አረቢያ ፍልስጤምን እውቅና ያልሰጡ ሁሉም ሀገራት ተመሳሳይ አዎንታዊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እና የፍልስጤም ህዝብ ሰላምን እና ህጋዊ መብቶችን የሚደግፉ አቋሞችን እንዲይዙ ጥሪያቸውን አጠናክራለች ብሏል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ በሴፕቴምበር ወር በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፍልስጤምን እንደ መንግስት እውቅና ለመስጠት ማቀዳቸውን ሐሙስ ዕለት አስታውቀዋል። ይህ ውሳኔ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላምን ለማምጣት እንደሚረዳ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው፣ ይህ እርምጃ “ሽብርተኝነትን መሸለም” እና “ሌላ የኢራን ተኪ ኃይል የመፍጠር አደጋ” እንዳለው በመግለጽ ውሳኔውን አውግዘውታል።
ፈረንሳይ የፍልስጤምን መንግስት እውቅና ለመስጠት የወሰነችው፣ በአውሮፓ ውስጥ ትልቁ የአይሁድ እና የሙስሊም ማህበረሰቦች መኖሪያ በመሆኗ፣ ሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የሚያግዝ ሊሆን ይችላል የተባለ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ140 በላይ የሚሆኑ የዓለም አገሮች ፍልስጤምን እንደ መንግስት እውቅና ሰጥተዋል ነው የተባለው።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ