ሐምሌ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) አባልነቷን ለማቋረጥ እየተዘጋጀች መሆኑ ታውቋል።
ይህ ውሳኔ የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ሲተቹዋቸው የነበሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የአሜሪካን ተሳትፎ የመቀነስ ሰፋ ያለ አቀራረብ አካል ነው ተብሏል።
ከዋይት ሀውስ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ “አሜሪካን ቀድሞ” በሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው መሠረት፣ በዩኔስኮ ውስጥ መቀጠል የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አያስጠብቅም ብለው ያምናሉ ነው ያሉት።
የድርጅቱ አንዳንድ ተግባራት እና አቋሞች ከአሜሪካ እሴቶች እና ፖሊሲዎች ጋር እንደማይጣጣሙ ተገልጿል።
ይህ ከአሜሪካ መውጣት፣ በ2026 ታህሳስ ወር ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደምም በአሜሪካ መንግስታት በተለያዩ ጊዜያት ዩኔስኮን ለቀው የመውጣት እና እንደገና የመቀላቀል ታሪክ አካል ነው ተብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር ከዩኔስኮ በተጨማሪ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ለምሳሌ ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እና ከተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት መውጣቱ ይታወቃል።
የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሬይ አዙላይ በውሳኔው የተጸጸቱ ቢሆንም፣ ድርጅቱ ለዚህ ሁኔታ ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአሜሪካ መውጣት በድርጅቱ የገንዘብ ምንጮች ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም፣ ዩኔስኮ የገንዘብ ምንጮቹን በማብዛት እና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ስራውን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል ነው የተባለው።
ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ዓለም አቀፍ ትብብርን በሚያበረታቱ ድርጅቶች ላይ ሊኖረው በሚችለው ተፅዕኖ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
አንዳንድ ተንታኞች የአሜሪካ መውጣት እንደ ቻይና ያሉ ሌሎች አገሮች በዩኔስኮ ውስጥ ያላቸውን ተፅዕኖ እንዲያሳድጉ ዕድል ሊሰጥ ይችላል ብለው ሲያምኑ፣ ሌሎች ደግሞ የአሜሪካ ጥቅም በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመሳተፍ እንጂ በመገለል ሊጠበቅ እንደማይችል ይከራከራሉ።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ