ሐምሌ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ሰሜን ኮሪያ ሶስተኛውን 5,000 ቶን የሚመዝነውን የቾይ ህየን (Choe Hyon) ክፍል የጦር መርከብ በገዢው ሰራተኞች ፓርቲ ምስረታ ቀን፣ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 10 ቀን ለማጠናቀቅ ማቀዷን አስታውቃለች። ይህ እርምጃ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የባህር ኃይልን የማጠናከር፣ ምናልባትም የሩሲያን ድጋፍ በማግኘት፣ እንዲሁም ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን ማድረስ የሚችሉ መድረኮችን የማብዛት ተነሳሽነት አካል ይመስላል ተብሏል፡፡
የመንግስት ሚዲያ የሆነው “ሮዶንግ ሲንሙን” ዛሬ ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም እንደዘገበው፣ “ሶስተኛውን የቾይ ህየን ክፍል አጥፊ የጦር መርከብ ግንባታ ለመጀመር ትናንት ሰኞ በናምፖ የመርከብ ግንባታ ግቢ ሰልፍ ተካሂዷል ነው የተባለው።”ሰሜን ኮሪያ ግንባታውን እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2026 ለማጠናቀቅ ዝርዝር የጊዜ ሰሌዳውን በሰልፉ ላይ አስታውቃ፣ ስራውንም ከዝግጅቱ በኋላ እንደጀመረች ጋዜጣው ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ የመጀመሪያውን 5,000 ቶን ክፍል የጦር መርከቧን “ቾይ ህየን” ባለፈው አመት ሚያዚያ 26 ቀን አስጀምራ ነበር። ሁለተኛው ተመሳሳይ ክፍል አጥፊ የጦር መርከብ በዚሁ አመት ግንቦት 21 ቀን የተጀመረ ቢሆንም፣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በአፈር ላይ ተጣብቆ በአለም አቀፍ ደረጃ መሳለቂያ ሆኖ ነበር።
በአፈር ላይ የተጣበቀው መርከብ ተነስቶ “ካንግ ኮን” (Kang Kon) የሚል ስያሜ ተሰጥቶት፣ ዳግም የማስጀመር ስነ ስርዓት የዘንድሮው ሰኔ 12 ቀን ተካሂዷል። በስነ ስርዓቱ ላይ በንግግራቸው፣ ኪም ጆንግ ኡን ከ2026 ጀምሮ በየዓመቱ ሁለት የቾይ ህየን ክፍል ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አጥፊ የጦር መርከቦችን ለማሰማራት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል፤ ይህም ሰፊ የባህር ኃይል ማጠናከሪያ ጥረቶች አካል ነው ተብሏል፡፡
ይህ አዲስ ይፋ የተደረገው የግንባታ እቅድ ከኪም ትዕዛዝ ጋር የሚጣጣም ይመስላልም ነው የተባለው፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ