👉የሰው ልጅ ክሊኒካዊ ሙከራ በጃፓን ተጀመረ‼️
ሐምሌ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ለመጀመሪያ ጊዜ የጠፉ ጥርሶችን በድጋሚ ማሳደግ የሚያስችል አዲስ መድኃኒት በጃፓን በሰው ልጆች ላይ ክሊኒካዊ ሙከራ መጀመሩ ታወቀ። ይህ አስደናቂ ግኝት የጠፉ ጥርሶች ያለ ተከላ (implants) ወይም ሰራሽ ጥርሶች (dentures) በተፈጥሯዊ መንገድ የሚያድጉበትን ዘመን እያቀረበ ነው ተብሏል፡፡
ይህ አዲሱ መድኃኒት የሚሰራው በልጅነት ጊዜ የጥርስ እድገትን የሚያቆም ፕሮቲንን በመግታት ነው። ይህን በማድረግም ሰውነት የራሱን ጥርስ የማሳደግ ተፈጥሯዊ ችሎታውን እንደገና እንዲያነቃቃ ይረዳል ነው የተባለው፡፡
መድኃኒቱ ከዚህ ቀደም በአይጦችና በፌሬቶች (ferrets) ላይ በተሳካ ሁኔታ ተሞክሯል የተባለ ሲሆን፤ በዚህም የጠፉ ጥርሶች በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ማደግ መጀመራቸው ተረጋግጧል። በአሁኑ ወቅት የሰው ልጅ ሙከራዎች በጃፓን በሚገኘው የኪዮቶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል እየተካሄዱ ሲሆን፣ ትኩረቱ የጠፉ ጥርሶች ባሏቸው ጎልማሶች ላይ ነው ተብሏል፡፡
እነዚህ ሙከራዎች ስኬታማ ከሆኑ፣ በመቀጠል በዘረመል ምክንያት ጥርስ በሌላቸው ህጻናት ላይ ሙከራዎች እንደሚደረጉ ተመላክቷል፡፡
ምንም እንኳን መድኃኒቱ በስፋት ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ጥቂት ዓመታት የሚቀሩ ቢሆንም፣ ይህ ግኝት በዘርፉ (regenerative medicine) ትልቅ ስኬት ሲሆን፣ የጥርስ ህክምናን ለዘላለም ሊያሻሽለው እንደሚችል ታምኖበታል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ