
ሐምሌ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ከባርሴሎና ታዋቂ የአዳጊዎች ማዕከል ፍሬ ውጤት የሆነው ዣቪ ሲመንስ ወደ ፓሪስ ሴንት ጄርሜ ካቀና በኋላ ነገሮች እንዳሰቡት እየሄዱለት ባለመገኘታቸው እና በቂ የጨዋታ ጊዜ እና የመሰለፍ እድልን ባለማግኘቱ ምክንያት ከአምና አንስቶ ፓሪስ ሴንት ጄርሜን በውሰት በመልቀቅ ሌፕዚግ ቤት ቆይታ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል። አምና ደግሞ ውሰት ውሉ ፒኤስ ጂዎች ቋሚ እንዲሆን መፍቀዳቸው የሚታወስ ነው።
ውሉ ቋሚ እንዲሆን ሌፕዚጎች እየታየ የሚጨመረውን 30 ሚሊዮን ዩሮ ሳይጨምር 50 ሚሊዮን ዩሮ በቀጥታ ወጪ እንዳደረጉም የሚታወስ ነው።
ዣቪ ሲመንስ ለ18 ወር ያክል ሬድ ቡል አሪና ስቴዲየም ቆይታ ማድረጉ አይዘነጋም።በነዚህ 18 ወራት ውስጥ ተጫዋቹ ያለውን አቅም በሚገባ አሳይቷል ፤ እያሳየም ይገኛል። በሌፕዚግ ማልያ ባደረጋቸው 60 ጨዋታዎች 15 ጎል ሲያስቆጥር 19 ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። በሌፕዚግ የሚያቆነው ኮንትራት እስከ 2027 የሚቆይም ይሆናል ተብሏል።
ሌፕዚጎች ተጫዋቹን ማቆየት ቢፈልጉም የቀጣይ አመት የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ቲኬትን መቁረጥ አለመቻላቸውን ተከትሎ ተጫዋቹ በመጪው ክረምት የዝውውር መስኮት ሌፕዚጎች እንደሚለቅ በተረጋገጠ ደረጃ መገለፁን ተከትሎ ክለቡም ከሱ ዳጎስ ያለ ሂሳብ ማለትም እስከ 70 ሚሊዮን ፓውንንደ ሊጠይቁ እንደሚችሉ ይገመታል።
ሲመንስ በዚህ አመት ብቻ ለክለብ እና ለሀገር በተሰለፈባቸው 31 ጨዋታዎች 9 ጎል አስቆጥሮ 6 ኳስ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።
ስሙ በስፋት ከአርሰናል እና ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ሲያያዝ የቆየ ተጫዋች መሆኑ ይታወቃል። ዩናይትድ ዩሮፓ ሉጉን ሳያሳኩ እንደ ሲመንስ አይነት ቁልፍ ተጫዋቾችን ለማስፈረም የሚያስችል ቁመና ላይ ይገኛሉ ተብሎ አይገመትም።
ከዛ ውጪ በዛው በቡንደስሊጋው ጥሩ አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች በማስኮብለል የሚታወቀው ባየርሙኒክ የጀማል ሙሲያላ ጉዳት አስገዳጅ የተጫዋች ግዢን እንዲያከናውኑ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ሲገለፆ የቆየው ባየርሙኒኮች ተጫዋቹን ለማስፈረም እንቅስቃሴዎችን ቢጀምሩም ተጫዋቹ ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ተሰምቷል።
ታዲያ በጀርመን ተአማኒነት ካተረፉ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ፍሎሪያን ፕሌተንበርግ የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ተጫዋቹን ለማስፈረም ይፋዊ ንግግሮችን መክፈታቸውን አረጋግጫለሁ ሲል ዘግቧል። ከክለቡ ጋር ድርድር ከመጀመራቸው በፊት ከተጫዋቹ ጋር ተነጋግረው በመጀመሪያ ከስምምነት ላይ መድረስ እንደሚፈልጉ ነው የፕሌተንበርግ መረጃ የሚያመላክተው።
እንደሚታወቀው አሰልጣኝ ኤኝዞ ማሬስካ አሁንም ነአጥቂ መስመራቸውን ለማጠናከር በዋናነት 10 ቁጥር ቦታ ላይ አንድ ተጫዋች ለማስፈረም ጥረት እንደሚያደርጉ መናገሩ አይዘነጋም።
የዚህ ክለብ አስፈሪ የሚባለው የፊት መስመራቸውን አሁንም ለማጠናከር በዚ ቦታ ሲመንስን ምርጫቸው አድርገዋል ተብሏል።
ሌላው የለንደን ክለብ አርሰናልም የተጫዋቹን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተሉ እንደሚገኙ ቢገለፆም በቼልሲ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ አይገኝም። አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አሁንም ስብስባቸው የጥልቀት ውስንነት አለበት ብሎ መናገሩ አንድም የቡድኑ አምበል ማርቲን ኦዴጋርድ ላይ ጥሩ ተተኪ ፤ ፉክክር ሊሰጥ የሚችል አቅም ያለው ተጫዋች ክለቡ ለማስፈረም ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ፍንጭ የሰጠ ነው። እንደሚታወቀው ከክሪስታል ፓላሱ ኤብሬቺ ኤዚ ጋር በበግል ጥቅማጥቅም ከስምምነት ላን መድረስ ቢችሉም የፓላስ 68 ሚሊዮን ፓውንድ የውል ማፍረሻ የመክፈል ግዴታ ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል። አሁን ታዲያ በአማራጭነት ሲመንስንም እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተገልጿል። ኤዜ 27 አመቱ ነው ፤ ሲመንስ በበኩሉ 23 መሆኑ ሌላው ተመራጭ እንዲሆን የሚዪስገድደው ሌላው ጉዳይ ነው።
የጀርመኑ ተነባቢ ጋዜጣ Bild ተጫዋቹ ቀዳሚ ምርጫው የፕሪሚየር ሊግ እግርኳስ ነው ብሎ ማስነበቡን ተከትሎ ሲመንስ መዳረሻው ለንደን መሆኑ እንደማይቀር አመላካች ተደርጎ የተወሰደ ጉዳይ ቢሆንም ወደ ምዕራቡ ወይስ ወደ ሰሜን ለንደን ወዴት ያቀናል የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የሚታይ ይሆናል።
በአጠቃላይ ይሄ ጥሩ አቅም ያለው የ22 አመቱ ኔዘርላንዳዊ ዣቪ ሲመንስን በ Technical ability ፤ Tactical flexibility እንዲሁም attacking versatility ይታወቃል ፤ ይሄን ክህሎት እና አቅሙን ይዞ የትኛውን የፕሪሚየር ሊግ ቡድን ይቀላቀላል የሚለው ጉዳይ በቀጣይ የእግርኳስ ቤተሰቡ የሚጠብቀው ጉዳይ ነው።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
ምላሽ ይስጡ