ሐምሌ 15 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደሚያመለክተው ውሾች የፓርኪንሰን በሽታን ምልክቶች ከመታየታቸው በፊት ለዓመታት በማሽተት መለየት የሚችሉ ሲሆን፣ ይህንንም እስከ 98% በሚደርስ ትክክለኛነት እንደሚያደርጉት ተገለጸ። ይህ ግኝት ለፓርኪንሰን በሽታ ቀደምት ምርመራ እና ህክምና አዲስ ተስፋ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
ፓርኪንሰን የነርቭ ሥርዓትን የሚያጠቃ እና ቀስ በቀስ እየተባባሰ የሚሄድ በሽታ ሲሆን፣ መንቀጥቀጥ፣ የሰውነት እንቅስቃሴ መዘግየት እና ሚዛን መዛባት በዋነኝነት ከሚታዩ ምልክቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ። በሽታው በቅድሚያ መታወቅ ህክምናን በጊዜ ለመጀመር እና የበሽታውን ሂደት ለመቀነስ ወሳኝ ሚና ይጫወታል ነው የተባለው፡፡
ጥናቱ እንደሚያመለክተው ውሾች በሰዎች አካል የሚወጡ ልዩ ሽታዎችን በመለየት የበሽታውን መኖር ማወቅ ይችላሉ የተባለ ሲሆን፤ይህ የውሾች አስደናቂ የማሽተት ችሎታ ከዚህ ቀደም የካንሰር እና የስኳር በሽታን በመለየት ረገድም ጥቅም ላይ ውሏል ነው የተባለው፡፡
ባለሙያዎች ይህ ግኝት ሰዎች ፓርኪንሰን በሽታ እንዳለባቸው ለማወቅ በሚደረገው ጥረት ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተስፋ ያደርጋሉ ተብሏል። በቀጣይ የሚደረጉ ጥናቶች ይህንን ዘዴ ወደ ክሊኒካዊ አሰራር ለማምጣት የሚያስችሉ መንገዶችን ይፈትሻሉም ነው የተባለው።
የውሾችን የማሽተት ችሎታ በመጠቀም የተሻሻሉ የምርመራ መሳሪያዎችን ማምረት ይቻል ይሆናል ተብሎ እንደሚታሰብ ተመላክቷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ