👉የብሔራዊ ሃዘን ቀን ታውጇልም ተብሏል
ሐምሌ 14 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በባንግላዲሽ ዋና ከተማ ዳካ በሚገኝ አንድ የኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የባንግላዲሽ አየር ኃይል ማሰልጠኛ ጄት ተከስክሶ ቢያንስ 19 ሰዎች ሲሞቱ ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል። አብዛኞቹ ተጎጂዎች ወጣት ተማሪዎች እንደሆኑ ተገልጿል። አገሪቱ ብሔራዊ የሐዘን ቀንን እንዳወጀችም ተሰምቷል።
ኤፍ-7 ቢጂአይ (F-7 BGI) የተሰኘው አውሮፕላን በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ከቀትር በኋላ 7 ሰአት ላይ ከፍ ካለ በኋላ፣ ከአስራ ሁለት ደቂቃ ገደማ በኋላ በዋና ከተማዋ ሰሜናዊ ክፍል በኡታራ ዲያባሪ አካባቢ በሚገኘው ማይልስቶን ትምህርት ቤት እና ኮሌጅ ካንቲን አቅራቢያ ተከስክሷል ሲል የኢንተር-ሰርቪስ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት (ISPR) ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የባንግላዲሽ ጋዜጣ ፕሮቶም አሎ እንደዘገበው ወታደራዊው አውሮፕላን አደጋው ሲከሰት በርካታ ወጣት ተማሪዎች በቦታው በነበሩበት ወቅት የምሳ ሰዓት ላይ ከትምህርት ቤቱ ካንቲን አጠገብ ተከስክሷል ብሏል ዘገባው። የመጀመሪያው የሟቾች ቁጥር አንድ ብቻ የነበረ ሲሆን፣ የእሳት አደጋና ሲቪል መከላከያ ዳይሬክተር ጀኔራል ብሪጋዴር ጀኔራል መሐመድ ዛሂድ ከማል ወደ ስፍራው ከደረሱና ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ከሰጡ በኋላ የሟቾች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል ነው የተባለው።
ነገ ማክሰኞም የብሔራዊ የሐዘን ቀን ታውጇል ነው የተባለው፡፡
የባንግላዲሽ ኤፍ-7 የቻይና ቼንግዱ ኤፍ-7 ዘመናዊ ስሪት ሲሆን እሱም በሶቪየት ሚግ-21 ላይ የተመሰረተ ነው ተብሏል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ጊዜ ያለፈበት ቢሆንም፣ ወጪ ቆጣቢነቱ እና ለአብራሪ ስልጠናና ለተገደበ የውጊያ ሚናዎች ተስማሚ በመሆኑ አገልግሎት ላይ ይገኛል ነው የተባለው።
ቻይና የመጨረሻዎቹን 16 የኤፍ-7 ቢጂአይ አውሮፕላኖችን ለባንግላዲሽ በ2013 ዓ.ም. ከሰጠች በኋላ ምርቱ ቆሟል ተብሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ