ሐምሌ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ኬንያዊቷ የረጅም ርቀት ሯጭ የሆነችው ሩት ጄፒንጌች በአለም አትሌቲክ ኢንቴግሪቲ ዩኒት ወይም የአለም አትሌቲክስ የውድድር እና ቁጥጥር ስርአት ባደረገው random test ወይም ድንገተኛ የቁጥጥር ስርአት Hydrochlorothiazide ወይም ሀይድሮክሎሮትዛይድ የተባለ አበረታች ንጥረ ነገር በሰውነቷ ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ አትሌቷን ላልተወሰነ ጊዜ ምንም አይነት ውድድሮች ላይ ከመሳተፍ ታግዳ እንድትቆይ ወስኗል።
ይህች አትሌት ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ በተደረገው የቺካጎ ማራቶን ላይ በኢትዮጵያዊቷ ትዕግስት አሰፋ ተይዞ የነበረውን የአለም ሪከርድ በማሻሻል እንዲሁም በታሪክ 2 ሰአት ከ10 ደቂቃ ባነሰ ጊዜ ውድድሯን ያጠናቀቀች የመጀመሪያዋ ሴት አትሌት መሆኗ የሚታወስ ነው። የገባችበት ሰአት 2 ሰአት ከ9 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ እስካሁን ድረስ በሴቶች ማራቶን የተመዘገበው ፈጣኑ ሰአት ሆኖ ይገኛል። ይህም ውጤት የአትሌቷ የአበረታች ንጥረ ነገር ጉዳይ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ያስመዘገበችው የአለም ሪከርድ ከአትሌቲክሱ መዝገብ ላይ እንዲወርድ ተደርጓል።
አትሌቷ በ2019 ኳታር ዶሀ ላይ በተከናወነው የአለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለሀገሯ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገብ የቻለች አትሌት መሆኗ የሚታወስ ነው።
ስለዚህ በሴቶች የማራቶን ሪከርድ አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ በጊዜያዊነት ወደ ጀግናዋ አትሌታችን ትዕግስት አሰፋ የሚመለስ ሲሆን 2 ሰአት ከ 11 ደቂቃ ከ 53 ሰከንድ የገባችበት የ2023ቱ የበርሊኑ ማራቶን እስከ ቅርብ ጊዜ በአትሌት ጄፒንጌች እስኪሻሻል ድረስ የአለም ፈጣኑ ሰአት እንደነበር የሚታወስ ነው። ትዕግሥት ሪከርዱን ከዚ በፊት በ2014 በኬንያዊቷ አትሌት ብሪጊድ ኮስጌይ ተይዞ የነበረውን የ2:14:04 ሰከንድን ከሁለት ደቂቃዎች በላይ በማሻሻል ሪከርዱን የግሏ ማድረጓ የሚታወስ ነው።
በሚካኤል ደጀኔ
__
ምላሽ ይስጡ