ሐምሌ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በታችኛው እግራቸው እብጠት ምክንያት በተደረገላቸው የህክምና ምርመራ፣ ሥር የሰደደ የደም ሥር እጥረት (Chronic Venous Insufficiency – CVI) እንዳለባቸው መረጋገጡን ዋይት ሀውስ አስታወቀ። ይህ የጤና እክል ደም ከእግር ወደ ልብ በትክክል እንዳይመለስ የሚያደርግ ሲሆን፣ በተለይም በእድሜ የገፉ ሰዎች ላይ የተለመደ እንደሆነ ተገልጿል።
የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮላይን ሊቪት እንደገለጹት፣ ፕሬዝዳንቱ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በታችኛው እግራቸው ላይ መጠነኛ እብጠት በማየታቸው የህክምና ምርመራ ተደርጎላቸዋል።
ምርመራውም ሥር የሰደደ የደም ሥር እጥረት እንዳለባቸው ያረጋገጠ ቢሆንም፣ ይበልጥ አሳሳቢ የሆኑ እንደ ጥልቅ ደም ስር መርጋት (Deep Vein Thrombosis – DVT) ወይም የደም ቧንቧ በሽታዎች (arterial diseases) አለመኖራቸውን የፕሬዝዳንቱ ሀኪም አረጋግጠዋል።
ይህ የጤና ሁኔታ አደገኛ እንዳልሆነና በአብዛኛው በ70 ዓመት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚታይ መሆኑን ሊቪት አስረድተዋል። የደም ሥር እጥረት የሚከሰተው በእግር ውስጥ የሚገኙት ደም ወደ ልብ የሚመልሱ ትናንሽ ቫልቮች በትክክል ሳይሰሩ ሲቀሩ ደም በእግር ውስጥ እንዲከማች ሲያደርግ ነው።
ምንም እንኳን ይህ ሁኔታ የፕሬዝዳንቱን አጠቃላይ ጤና የማያሳስብ ቢሆንም፣ የህክምና ባለሙያዎች እብጠትን ለመቀነስ እግርን ከፍ ማድረግ፣ የእግር እንቅስቃሴ ማድረግ እና ክብደትን መቆጣጠርን የመሳሰሉ የመፍትሄ እርምጃዎችን እንደሚመክሩ ይታወቃል።
የፕሬዝዳንቱ የጤና ሁኔታ በቅርበት ክትትል እንደሚደረግበትም ተመላክቷል።

__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ