በጨረቃ ላይ መኖር ይቻል ይሆን?
ሐምሌ 11 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ሳይንቲስቶች ከጨረቃ አቧራ (regolith) ውኃና ኦክሲጅንን በፀሐይ ብርሃን ብቻ ማውጣት የሚያስችል አዲስ ዘዴ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። ይህ ግኝት በጨረቃ ላይ የሰው ልጅ ቋሚ መኖሪያ ለመገንባት የሚያስችሉ ሀብቶችን ለማምረት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
የቻይና የሳይንስ አካዳሚ (Chinese Academy of Sciences) ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፣ በቻንግ-5 (Chang’e-5) ተልዕኮ ወደ ምድር ከመጣው የጨረቃ አፈር ናሙና በመጠቀም የፀሐይ ብርሃንን በማተኮር አፈሩን ከ900 ዲግሪ ሴልሲየስ በላይ አሞቀውታል። ይህ ከፍተኛ ሙቀት በጨረቃ አፈር ውስጥ የሚገኘውን ሃይድሮጂን ከሌሎች ንጥረ ነገሮች ጋር እንዲዋሃድ በማድረግ የውኃ ትነት እንዲለቀቅ አድርጓል ነው የተባለው።
የተለቀቀው የውኃ ትነትም ተሰብስቦ ወደ ፈሳሽ ውኃ ተቀይሯል። ከዚህም በላይ በዚሁ ሂደት ውስጥ ካርቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) በመጨመር ለትንፋሽ የሚያገለግል ኦክሲጅን እና ለሮኬት ነዳጅ የሚሆን ሃይድሮጂንም ማመንጨት ተችሏል ነው የተባለው።
ይህ ዘዴ በጨረቃ ላይ ቀጣይነት ያለው የሰው ልጅ መገኘት እንዲኖር ትልቅ አስተዋፅዖ ይኖረዋል ተብሎ የተገመተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከምድር ወደ ጨረቃ አንድ ሊትር ውሃ ማጓጓዝ ወደ 33,000 የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስወጣ ሲታሰብ፣ በጨረቃ ላይ ውሃ ማምረት ወጪን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ ይህ ዘዴ በላብራቶሪ ደረጃ ስኬታማ መሆኑን ቢያረጋግጡም፣ በጨረቃ ገጽ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አንዳንድ ፈተናዎች እንዳሉ ጠቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የጨረቃ ላይ ከፍተኛ የሙቀት ለውጥ፣ ከፍተኛ ባዶነት (vacuum) እና ጠንካራ የፀሐይ ጨረር ናቸው ተብሏል።
በተጨማሪም የጨረቃ አፈር ውህድነት ወጥ አለመሆኑ እና በአሁኑ ወቅት የሚመነጨው የውሃና ኦክሲጅን መጠን ለሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ በቂ አለመሆኑ ተጠቅሷል።
ቢሆንም፣ ሳይንቲስቶቹ ቴክኖሎጂውን በማሻሻል እና ለጨረቃ ሁኔታዎች ተስማሚ የሆኑ መሳሪያዎችን በመንደፍ እነዚህን ተግዳሮቶች ማለፍ እንደሚቻል እምነት አላቸው ተብሏል። ይህ ግኝት በጨረቃ ላይ ዘላቂ ሰፈራ ለመገንባት እና ወደ ሌሎች ፕላኔቶች ለሚደረጉ የጠፈር ጉዞዎች እምቅ ሀብት መፍጠር እንደሚያስችል ሳይንቲስቶች እየገለጹ ነው።

__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ