ሐምሌ 10 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ) – የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (MIT) ተመራማሪዎች፣ ከምድረበዳ አየር ንፁህ የመጠጥ ውሃ ማውጣት የሚችል አብዮታዊ የፀሐይ ኃይል ፓነል ቴክኖሎጂን በማልማት ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገባቸው ተዘገበ። ይህ ፈጠራ በተለይ ለደረቃማ አካባቢዎች እና ለዓለም አቀፍ የውሃ እጥረት ችግር ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ሳይንሳዊ ማህበረሰቡ እያስመሰከረ ነው።
ይህ ልዩ ፓነል ምንም ዓይነት ውጫዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ ወይም ሰፊ የውሃ ቧንቧ መረብ ሳያስፈልገው፣ በቀጥታ በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት በአየር ላይ የሚገኘውን የእርጥበት ትነት በመሳብ ወደ ንፁህ ፈሳሽ ውሃ የመቀየር አቅም አለው ነው የተባለው።
የቴክኖሎጂው ቁልፍ ሚስጥር “ሜታል-ኦርጋኒክ ፍሬምዎርክ” (Metal-Organic Frameworks – MOFs) የሚባሉ ልዩ ቁሳቁሶችን መጠቀም ነው ተብሏል። እነዚህ ሜታል-ኦርጋኒክ ፍሬምዎርኩ እጅግ በጣም ደረቅ በሆነ አየር ውስጥ እንኳን የውሃ ሞለኪውሎችን የመሳብ እና የማቆየት ከፍተኛ ችሎታ አላቸው ተብሏል። ፓነሉ የፀሐይን ኃይል በመጠቀም ሜታል-ኦርጋኒክ ፍሬምዎርኩ ውሃውን እንዲለቅ በማድረግ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያመነጫል ነው የተባለው።
በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ እጥረት በሚያጋጥማቸው ወቅት፣ ይህ ቴክኖሎጂ በተለይም በረሃማና ከማንኛውም የውሃ ምንጭ ርቀው ለሚኖሩ ማህበረሰቦች ህይወት አድን ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ውሃን ለማምረት የኃይል ማመንጫዎች ወይም ውስብስብ የቧንቧ ዝርጋታ ስለማይፈልግ፣ በገጠር፣ በድንገተኛ አደጋ ጊዜያት ወይም በልማት ባልተዳበሩ አካባቢዎች ወዲያውኑ አገልግሎት መስጠት ይችላል ተብሎለታል።
የፀሐይ ኃይልን ስለሚጠቀም ለአካባቢ ተስማሚ ሲሆን፣ ከውሃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ጋር ተያይዞ የሚመጣን ከፍተኛ የኃይል ፍጆታ እና የካርበን ልቀትን ይቀንሳልም ተብሏል።
በቴክኖሎጂው አማካኝነት የተገኘው ውሃ በኬሚካሎች ያልተበከለ እና ለመጠጥ ተስማሚ መሆኑ ተረጋግጧል የተባለ ሲሆን፤ይህ የኤም.አይ.ቲ. ስኬት የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ድንበርን የገፋ ሲሆን፣ የሰው ልጅ ለወደፊት የውሃ ሀብቱን በብቃት እንዲያስተዳድር እና ዘላቂ የህልውና መፍትሄዎችን እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት በሰፊው እየተነገረ ነው።
ተመራማሪዎቹ ቴክኖሎጂውን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እና የማምረቻ ወጪውን ለመቀነስ ጥረታቸውን እንደቀጠሉ መሆናቸውም ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን 📞
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 🔊 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ