ሐምሌ 08 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ለዓመታት የሳይንስ ሊቃውንትን ትኩረት ሲስብ የቆየው የአፍሪካ ቀጣናዊ ለውጥ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
አፍሪካ አህጉር ቀስ በቀስ እየተሰነጠቀችና በመካከሏ አዲስ ውቅያኖስ የመፍጠር ሂደት ላይ እንደምትገኝ የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ጥልቅ ስምጥ ሸለቆዎች በምስራቅ አፍሪካ በኩል ተፈጥረው እየሰፉ ይገኛሉ ተብሏል።
ይህ ስምጥ ሸለቆ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመሄድ በምስራቅ አፍሪካ በኩል የሚገኘውን ክፍል ከቀሪው አህጉር የመለየት አዝማሚያ እያሳየ መሆኑ እየተዘገበ ነው።
ጂኦሎጂስቶች እንደሚሉት፣ ይህ ሂደት የሚሊዮኖች ዓመታት የሚወስድ ሲሆን፣ በመጨረሻም ሁለቱን የአፍሪካ ክፍሎች የሚለይ አዲስ ውቅያኖስ ይፈጥራል ነው የተባለው።
ይህ ተፈጥሯዊ ሂደት በምድር ንጣፍ (tectonic plates) እንቅስቃሴ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን፣ የአፍሪካ ታርጋ (African Plate) ከሌሎች ታርጋዎች ጋር በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሚፈጠር መሆኑ ተመላክቷል።
በምስራቅ አፍሪካ ያለው ስምጥ ሸለቆ ከቀይ ባህር ወደ ደቡብ እየተጓዘ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ የመሰንጠቅ ሂደት በአካባቢው የመሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴ እንዲበዛም አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው የተባለው።
ይህ አዲስ ውቅያኖስ ሲፈጠር፣ የአፍሪካ ካርታ በአዲስ መልክ እንደሚቀየርና በርካታ ተፈጥሯዊና ጂኦግራፊያዊ ለውጦች እንደሚከሰቱም የሳይንስ ሊቃውንት ይገልጻሉ።
ይህ ክስተት ለአካባቢው ሥነ-ምህዳር፣ የአየር ንብረት እና ለሰው ልጅ ሰፈራ አዲስ ተጽእኖዎች ሊኖሩት እንደሚችሉም ይጠበቃል ተብሏል።
ይህን ሂደት ለመከታተል እና ሳይንሳዊ ምርምሮችን ለማካሄድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሳይንቲስቶች በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙም ተመላክቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ