ሐምሌ 07 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተጀመረው ከፍርድ ቤቶች ጋር የመስራት ሂደት በአመት 1ሺሕ 598 የፍቺ ውሳኔዎችንና 127 የጉዲፈቻ አገልግሎት መስጠቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
በኤጀንሲ የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ዳይሬክተር ቤዛዊት ብርሃኔ ከፍርድ ቤቶች ጋር በጋራ በሚሰራ ስራ ተቋሙ ከታህሳስ ወር ጀምሮ የፍቺና የጉዲፈቻ ሁነቶችን ጉዳዩ በሚከናወንበት ፍርድ ቤቶች ባለሙያ መድቦ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ኤጀንሲው ከፍርድ ቤቶች ጋር በጀመረው የጋራ ስራ አሁን ላይ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች እና በሸሪዓ ፍርድ ቤት ያሉትን ሁነቶች ቦታው ድረስ ሄዶ በመመዝገብ በከተማ ደረጃ የፍርድ ቤት ሁነቶችን በመረጃ ማቆየት እየተቻለ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በመሆኑም በሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች 1ሺ 598 የፍቺ ውሳኔዎች እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ ብቻ በሚከናወነውን የጉዲፈቻ አገልግሎት ደግሞ 127 ያህል አገልግሎት መመዝገቡን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የሸሪሃ ፍርድ ቤት 12ኛ ፍርድ ቤት ሆኖ ሁነት የሚመዘገብበት መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሯ፣ የጋብቻና የፍቺ ሁነቶች እንደተመዘገቡ አስታውቀዋል። በመሆኑም ስራው ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከተያዘው ሐምሌ ወር ድረስ 1ሺ 228 ጋብቻ እና 11 ፍቺን ኤጀንሲው በቦታው ተገኝቶ መመዝገቡን ነው የተናገሩት።
ኤጀንሲው በ11ዱም ክፍለ ከተሞች የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶችና በሸሪሃ ፍርድ ቤቶች በሚሰጠው አገልግሎት በፍርድ ቤቶቹ በኩል የመረጃ አለመሟላት ተግዳሮት እንደፈጠረበት የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ስራው የመጀመሪያ እንደመሆኑ ከስር ከስር በመነጋገር ለመፍታት እየተሞከረ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ከፍርድ ቤቶች ወደ ወረዳዎች መረጃ በመውሰድ የሁነት ምዝገባ ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ለመጨመር ኤጀንሲው ቦታው ድረስ ሄዶ ሁነቶችን መመዝገቡ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ