ሐምሌ 05 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በቻይና ሰማይ ላይ እጅግ ያልተለመደ እና አስገራሚ የተፈጥሮ ክስተት ታይቷል። “ሰንዳግስ” (Sundogs) በመባል የሚታወቀው ይህ ብርቅዬ ክስተት፣ ሰማዩ ላይ አምስት ፀሐዮች የበሩ እንዲመስል አድርጓል። ይህ ክስተት በብዙ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንቅትና አግራሞት ፈጥሯል።
“ሰንዳግስ” ወይም “ፓርሄሊያ” (Parhelia) በመባልም የሚታወቀው ይህ ክስተት፣ በከባቢ አየር ውስጥ በሚገኙ የበረዶ ክሪስታሎች አማካኝነት የፀሐይ ብርሃን ሲንፀባረቅ የሚፈጠር ኦፕቲካል ቅዠት ነው ተብሏል።
እነዚህ የበረዶ ክሪስታሎች እንደ ፕሪዝም ሆነው የፀሐይን ብርሃን ስለሚበትኑ፣ ከእውነተኛዋ ፀሐይ ጎን ለጎን ተጨማሪ የብርሃን ነጥቦች እንዲታዩ ያደርጋሉ። እነዚህ ነጥቦች እንደ ተጨማሪ ፀሐዮች ሊታዩ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ይህ ክስተት የሚታየው በከባቢ አየር ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ባለ ስድስት ጎን የበረዶ ክሪስታሎች ሲኖሩ እና የፀሐይ ብርሃን በእነሱ ውስጥ ሲያልፍ ነው። ብዙውን ጊዜ የሚታየው ፀሐይ ከአድማስ ጋር ስትጠጋ ወይም በጣም ስትቀርብ ሲሆን፣ የሙቀት መጠኑ ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች በብዛት እንደሚስተዋል መረጃዎች ያመላክታሉ።
በቻይና የተከሰተው ይህ ልዩ “ሰንዳግስ” ክስተት፣ የፀሐይ ብርሃን በተለያዩ አቅጣጫዎች በመበተኑ ምክንያት አምስት የሚሆኑ የፀሐይ ምስሎች በተመሳሳይ ሰዓት በሰማይ ላይ ታይተዋል። ይህን አስደናቂ ትዕይንት በብዙ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች መመልከት ችለዋል ነው የተባለው።
የሜትሮሎጂ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ ይህ ክስተት ምንም አይነት አስደንጋጭ ወይም አደገኛ ሁኔታ የሚያመለክት ሳይሆን፣ የተለመደ የተፈጥሮ ክስተት ነው ብለዋል። ሆኖም፣ በአንድ ጊዜ በርካታ የፀሐይ ምስሎች መታየታቸው እጅግ ያልተለመደ እና አድናቆትን የሚቸር ሆኖ ተገኝቷል።
ይህ ክስተት የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖ በርካታ ፎቶዎችና ቪዲዮዎች ተጋርተዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ