ሐምሌ 04 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ “ሚኒባስ” ታክሲዎች ያለ ረዳት መንቀሳቀስ እንደማይችሉ እና ተሳፋሪን ማጉላላት በህግ እንደሚያስቀጣቸው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ገልጿል፡፡
በቢሮው በኩል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የተሰራ ቢሆንም ችግሩ አሁንም እንደሚስተዋል በቢሮው የህዝብ ትራንስፖርት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ጌትነት ታመነ ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡
ረዳት የሌላቸው አሽከርካሪዎች በአሰራር ሂደት መሰረት ‹ተሳፋሪን ማጉላላት› በሚል እንደሚከሰሱ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ ቢሮው እስካሁን የማስተማርና እርምጃ የመውሰድ ስራ የሰራ ቢሆንም አንዳንድ አከባቢዎች አሁንም ክፍተቶች እንደሚስተዋልባቸው አመላክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ እንደ አስገዳጅ ስራ በማሰራት በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በተደረገ የቁጥጥር ስራ እንዲሁም ማህበረሰቡ 9417 በሚያደርሰው ጥቆማ መሰረት 55 አሽከርካሪዎች ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደባቸው አቶ ጌትነት ገልጸዋል፡፡
ስራው በትብብር የሚሰራ ስለሆነ የትራፊክ ፖሊሶች ቅድሚያ ለሰልፍና ለአደጋው አጋላጭ ለሆኑ ነገሮች ትኩረት ስለሚሰጡ እንጅ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ቢሮው የሚመለከታቸውን አካላት አሰማርቶ እንደሚሰራና ህብረተሰቡም የሚያስተውለውን የአሰራር ክፍተት በ9417 መጠቆም እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
ደንቡን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ቅጣት እንደሚጣልባቸው አቶ ጌትነት አስታውቀዋል፡፡
ምላሽ ይስጡ