ሐምሌ 02 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ)፣ በአሁኑ የአሜሪካ አስተዳደር የሚተገበሩ የታሪፍ ውሳኔዎች መዘግየቶች ዓለም አቀፍ የንግድ አለመረጋጋትን እያባባሱ መሆኑን አስጠንቅቋል። ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው፣ የአሜሪካ የንግድ ፖሊሲዎች በሚቀጥሉት ወራቶች ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ግልጽ ባለመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና መንግስታት የእቅድ ማውጣት ችግር እየገጠማቸው ባለበት ወቅት ነው ተብሏል።
የተመድ የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ባወጣው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፣ ታሪፍን በተመለከተ ያሉ ያልተወሰኑ ሁኔታዎች የንግድ ልውውጥን እያቀዘቀዙና በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ጭንቀት እየፈጠሩ ነው ተብሏል። ኢንቨስተሮችም በአሜሪካ የንግድ አጋሮች ላይ ሊጣሉ በሚችሉ አዳዲስ ታሪፎች ወይም ነባር ታሪፎች ላይ በሚደረጉ ለውጦች ምክንያት ጥንቃቄ እያደረጉ ነው።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ የንግድ ፖሊሲዎች ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም በዓለም ዙሪያ ባሉ ሀገራት የንግድ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በተለይም ታላላቅ የንግድ አጋሮች አሜሪካ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች በቅርበት እየተከታተሉ ሲሆን፣ የራሳቸውን የንግድ ስትራቴጂዎች በማስተካከል ላይ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
ተመድ ይህንን በማስጠንቀቅ፣ የንግድ ፖሊሲዎች ግልጽና ሊተነበዩ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው አሳስቧል። ይህም ዓለም አቀፍ ንግድ እንዲያብብ እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት እንዲኖር ወሳኝ መሆኑን አስምሮበታል።
ምላሽ ይስጡ