ሐምሌ 01 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ስፔን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታዋን ከታዳሽ ኃይል ምንጮች በማግኘት ታሪካዊ ምዕራፍ አስመዘገበች።
ይህ ስኬት ሀገሪቱ በንፁህ ኃይል ሽግግር ሂደት ውስጥ የደረሰችበትን ከፍተኛ ደረጃ የሚያመላክት ነው ተብሎላታል።
የስፔን ብሔራዊ የኤሌክትሪክ አውታር ኦፕሬተር ባወጣው መረጃ መሰረት፣ ለተወሰነ ጊዜ ያህል፣ ስፔን የሚያስፈልጋትን አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ከንፋስ፣ ከፀሐይ፣ ከውሃ እና ከሌሎች ታዳሽ ምንጮች ሙሉ በሙሉ ማግኘት ችላለች ነው የተባለው።
ይህም ስፔን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና ከቅሪተ አካል ነዳጆች ጥገኝነት ለመላቀቅ በምትከተለው የፖሊሲ ውጤት ነው ተብሎላታል።
በርካታ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች እና የፀሐይ ፓነል እርሻዎች በመገንባታቸው፣ ሀገሪቱ በንፁህ ኃይል ምርት ረገድ ከዓለም ግንባር ቀደም አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ አስችሏታል ነው የተባለው።
ይህ የስፔን ስኬት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ትልቅ ተነሳሽነት መሆኑ ተመላክቷል። አንድ ትልቅ የአውሮፓ ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በታዳሽ ኃይል መብራት መቻሉ፣ ንፁህ ኃይል የዘመናዊ ኢኮኖሚዎችን ፍላጎት ማሟላት እንደሚችል በተግባር ያሳያል ነው የተባለው።
ይህ ደግሞ ሌሎች ሀገራት ወደ ታዳሽ ኃይል እንዲሸጋገሩ የሚያበረታታ ሲሆን፣ የአለምን የካርበን ልቀት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ነው የተባለው።
ምላሽ ይስጡ