ሐምሌ 02 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በአፍጋኒስታን በሚገኙ የሴቶችና ልጃገረዶች መብቶች ላይ ከፍተኛ ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በታሊባን ከፍተኛ መሪና በዋና ዳኛቸው ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱን አስታወቀ።
ፍርድ ቤቱ እንዳስታወቀው ታሊባን ልጃገረዶችንና ሴቶችን ከመሰረታዊ መብቶቻቸው በከፍተኛ ሁኔታ የሚነፍጉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ አድርጓል ብሏል።
ዝርዝር መረጃው እንደሚያመለክተው፣ የ ICC ዳኞች ታሊባን በአፍጋኒስታን ስልጣን ከያዘ በኋላ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን በህብረተሰቡ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክሉ፣ ትምህርትን የሚነፍጉ እና ነጻነታቸውን የሚገድቡ በርካታ አዋጆችንና ደንቦችን ማውጣቱን ገልጾ፤ እነዚህ ድርጊቶች የሰብዓዊ መብቶች ከባድ ጥሰቶች እንደሆኑ ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
የ ICC ዋና አቃቤ ህግ ካሪም ካን ለረጅም ጊዜ በአፍጋኒስታን ውስጥ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ሲመረምሩ ቆይተዋል። ይህ የእስር ማዘዣ መውጣት የታሊባን ባለስልጣናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚፈጽሟቸው ጥሰቶች ተጠያቂ መሆናቸውን የሚያሳይ ጠንካራ መልዕክት ተብሎ ታይቷል።
የታሊባን መንግስት እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ይፋዊ ምላሽ አልሰጠም። ይሁን እንጂ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይህንን የ ICC ውሳኔ በደስታ ተቀብለውታል ነው የተባለው፡፡
በእስር ማዘዣው የተካተቱት የታሊባን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስም እስካሁን ይፋ ያልተደረገ ቢሆንም፣ የፍርድ ቤቱ እርምጃ ታሊባን በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያለውን አቋም ይበልጥ እንደሚያወሳስበው ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አፍጋኒስታን ውስጥ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ በተለይም የሴቶችና ልጃገረዶች መብት ጉዳይ አሁንም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዋነኛ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል።
ምላሽ ይስጡ