ሰኔ 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በዩኒስኮ የተመዘገበው የአክሱም ሀውልትና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶች ለመጎብኘት ወደ አክሱም ከተማ የሚሄዱ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የአክሱም ከተማ የባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ተዳክሞ የነበረው የአክሱም ከተማ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከሰላሙ ስምምነት በኋላ ዳግም እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ተመለሶ የተዳከመበት ሁኔታ መፈጠሩን የፅ/ቤቱ የጎብኚዎች አስተባባሪ አቶ ኪዱ ተጠምቀ ተናግረዋል፡፡
ካሁን ቀደም በሚሊዮን የሚቆጠር ገቢ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ሀገርና የሐገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ኪዱ አሁን ላይ ባልታወቀ መልኩ ጎብኚዎች እንደሌሉ አክለዋል፡፡
በከተማዋ የፀጥታ ችግር አለመኖሩን እንዲሁም ጎብኚዎችን ሊያስቀር የሚችል ሌላ ምክንያት ሊኖር አይችልም ያሉ ሲሆን ምክንያታቸውን ግን የማጥራት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡
የአክሱም ሀውልት ጥገና በተመለከተ እስካሁን የተጀመረ ነገር የለም ያሉ ሲሆን በከተማው በቱሪዝም ዘርፉ ተደራጀተው የነበሩ ከ20 የሚበልጡ ማህበራት አሁን ላይ የሚያገኙት ገቢ ባለመኖሩ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡
በአክሱም ከተማ የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነሱ ምክንያት ጥናት እንዲደረግ ከክልሉ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የአክሱም ሀውልት የአለም ቅርስ በመሆኑ ሊጠበቅ ይገባል ያሉ ሲሆን ከዚህ ጋር በተገናኘም ጎብኚዎች ለምን ቀነሰ የሚለዉን ነገር ማጥራት እና ዳግም ጎብኚ ወደ ከተማ እንዲመጣ ማድረግ ላይ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በመዲና አውሰይድ
ምላሽ ይስጡ