ሰኔ 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ለ57ሺህ ታዳጊ ወጣቶች የክረምት የስፖርት ስልጠና ሊሰጥ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል።
ቢሮው ከያዝነው ሰኔ ወር ጀምሮ ምዝገባ ጀምሯል በማለት በሁሉም ክፍለ ከተማ ያሉ ታዳጊ ወጣቶችን የክረምት ስልጠና ለመስጠት ዝጅግት ስለመደረጉ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የማእከላትና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ባዩ ለጣቢያችን ገልጸዋል።
ስልጠናው በበጎ ፈቃደኝነት የሚከናወን መርሃግብር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህም ምክንያት ለሁሉም ሰልጣኞች በነጻ እንደሚሰጥም ነው የገለጹት። ታዳጊዎቹ በፈለጉት ስፖርት አይነት በነጻ ስልጠና እንደሚወስዱ የተገለጸ ሲሆን ማህበረሰቡ በያለበት ወረዳና ክፍለከተማ ልጆቹን ማስመዝገብ ይችላል ሲሉ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።
በየስፖርት አይነቱ አሰልጣኞችና የመሰልጠኛ ስፍራዎች መመቻቸታቸውንና እስከ መስከረም ወር ድረስ ታዳጊዎች በእረፍት ጊዜያቸው መሳተፍ እንደሚችሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ 57ሺህ ሰልጣኞች እስከሚሞሉ ቢሮው ተቀብሎ እንደሚያሰለጥን አክለዋል።
የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ለታዳጊዎችና ወጣቶች ሁለንተናዊ ስፖርት መትጋት ዋነኛ አላማው ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ መሰል በጎ ተግባራትን በየአመቱ እንደሚያስቀጥሉም ተናግረዋል።
በስንታየሁ አለማየሁ
ምላሽ ይስጡ