ሰኔ 28 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ሀማስ በአሜሪካ ለተደገፈው የጋዛ የተኩስ አቁም ሀሳብ ለአሸማጋዮች “አዎንታዊ ምላሽ” መስጠቱን አስታውቋል፤ ይህም ለ21 ወራት ያህል የዘለቀው ግጭት መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል የሚል ተስፋ ፈጥሯል።
የፍልስጤም ቡድን “አዎንታዊ መንፈስ” እና ወዲያውኑ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የመጨረሻ ህዝባዊ ይሁንታ አሁንም በመጠባበቅ ላይ ነው ተብሏል።
በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተመራው የ60 ቀናት የተኩስ አቁም እቅድ፣ ሀማስ በእጁ የያዛቸውን የእስራኤል ታጋቾች (ህይወት ያላቸውንና አስከሬኖችን ጨምሮ) በደረጃ መልቀቅን፣ በምላሹም በእስራኤል እስር ቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞችን መለቀቅን ያካትታል ነው የተባለው።
ስምምነቱ በጋዛ ላይ የሚካሄደውን የቦምብ ጥቃት ማቆም እና ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ ወደተከበበው ግዛት እንዲገባ መፍቀድን ያጠቃልላል ተብሎለታል።
ሀማስ አርብ ዕለት ለኳታር እና ግብፅ አሸማጋዮዎች ምላሹን ማስረከቡን ገልጾ፣ “ይህን ማዕቀፍ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ የድርድር ዙር ወዲያውኑ ለመጀመር” ዝግጁ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል።
ይሁን እንጂ ከድርድሩ ጋር ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚያመለክቱት ሀማስ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ግልጽ ቋንቋ እና ዋስትናዎችን ጠይቋል፤ በተለይም ጦርነቱን በዘላቂነት የማቆም እና የእስራኤል ኃይሎች ከጋዛ ሙሉ በሙሉ የመውጣት ጉዳዮች ላይ ነው ተብሏል።
ሀማስ የመጀመሪያው የተኩስ አቁም ወደ ሙሉ ግጭት ማቆም እንደሚመራ በተከታታይ ዋስትናዎችን ሲጠይቅ ቆይቷል፤ ይህ ደግሞ በቀደሙት የድርድር ዙሮች ላይ የአለመግባባት ነጥብ ሆኖ ቆይቷል።
የእስራኤል ሚዲያዎች ቅዳሜ ማለዳ ላይ እስራኤል የሀማስን ምላሽ መቀበሏን እና ይዘቱን እየመረመረች መሆኑን ዘግበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር በዋሽንግተን እንደሚገናኙ ይጠበቃል፤ ሆኖም እቅዱን በይፋ አላፀደቁም።
በጌታሁን አስናቀ
ምላሽ ይስጡ