ሰኔ 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)ኢትዮጵያ በመጪው የመስከረም ወር የአባይ ወንዝ ታላቁን ህዳሴ ግድብ (GERD) ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ስትሆን፣ ይህ ሜጋ ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘንድ ሰፊ ሽፋን እያገኘ ነው።
በተለይም ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙትን ግብፅንና ሱዳንን የሚያሳስብ በመሆኑ፣ የውጭ ሀገር የዜና ተቋማት የሁኔታውን የቅርብ ጊዜ እድገቶች በትኩረት እየዘገቡ ነው።
ሮይተርስ (Reuters) ባወጣው ዘገባ መሰረት፣ ግብፅ ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠን ላይ ሊያስከትል በሚችለው ተፅዕኖ ከፍተኛ ስጋት ያላት ሲሆን፣ በተደጋጋሚ ጊዜያት ዓለም አቀፍ ሽምግልና እንዲደረግ ጥሪ አቅርባለች። ሱዳንም በበኩሏ ከግድቡ የሚገኘውን ጥቅም የምትፈልግ ቢሆንም፣ የውሃ ደህንነቷ እንዳይጎዳ የጋራ ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥታለች። የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ግድቡ ያለ ስምምነት መሞላቱና ሥራ መጀመሩ በቀጠናው ላይ አለመረጋጋት ሊፈጥር እንደሚችል በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ሲገልጹ መቆየታቸው ተዘግቧል።
አልጀዚራ (Al Jazeera) በበኩሉ፣ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል በተደረጉት በርካታ የድርድር ዙሮች ላይ ትኩረት አድርጎ ዘግቧል። ድርድሮቹ በውሃ ሙሌትና በአሰራር ደንቦች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የመጨረሻ ስምምነት ላይ አለመደረሱ የውጭ ሚዲያዎችን ቀልብ ስቧል።
በርካታ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ የዩናይትድ ስቴትስ እና የአፍሪካ ህብረት በሽምግልና ሙከራዎች ውስጥ ተሳትፈዋል ነው የተባለው።
የቢቢሲ (BBC) ዘገባዎች የኢትዮጵያን አቋም ሲያስረዱ፣ ግድቡ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ልማት እና ለኃይል ፍላጎት ወሳኝ መሆኑን ይጠቅሳሉ። ኢትዮጵያ ከግድቡ የምታገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል በሀገር ውስጥ ያለውን የኃይል እጥረት ከማቃለሉም በላይ፣ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንደምትችል ትገልጻለች ብሏል በዘገባው። የኢትዮጵያ መንግስት ግድቡን የአፍሪካ የህዳሴ እና የልማት ምልክት አድርጎ እንደሚመለከተው የውጭ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የአባይ ግድብ ምረቃ በቀጠናው ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለል የቆየውን የውሃ ንትርክ አዲስ ምዕራፍ ሊከፍት እንደሚችል የሚጠበቅ ሲሆን፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ምላሽ ይስጡ