ሰኔ 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በናራ ሜዲካል ዩኒቨርሲቲ (Nara Medical University) በፕሮፌሰር ሂሮሚ ሳካይ (Prof. Hiromi Sakai) የሚመራ የጃፓን ተመራማሪዎች ቡድን ሁለንተናዊ ሰው ሰራሽ ደም ፈጥረዋል።
ይህ አዲስ ግኝት ከጥቅም ጊዜ ያለፈባቸው ለጋሽ ደሞች የተገኘ ሲሆን፣ ኦክስጅንን የሚሸከም ሄሞግሎቢን (hemoglobin-based oxygen-carrier) በተከላካይ ሽፋን ውስጥ ተዘግቶ የተሰራ ነው ተብሏል።
ይህ ሰው ሰራሽ ደም ምንም ዓይነት የደም አይነት የለውም፤ይህም የተኳሃኝነት ምርመራ የማድረግን አስፈላጊነት ያስቀራል፣ እንዲሁም እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በክፍል ሙቀት ውስጥ ሊከማች ይችላል፤በፍሪጅ ውስጥ ከተቀመጠ ደግሞ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል ነው የተባለው።
በማርች 2025፣ በ16 ጤናማ ጎልማሶች ላይ የክሊኒካዊ ደህንነት ሙከራዎች ተጀምረዋል። እነዚህ ተሳታፊዎች የደም ምትክ የሆነውን ይህን ሰው ሰራሽ ደም ከ100-400 ሚሊ ሊትር መጠን የተሰጣቸው ሲሆን፣ የደህንነቱን እና የመጀመሪያ ደረጃ ውጤታማነቱን ለመገምገም ታስቦ ነው።
ቀደም ሲል በ2022 የተደረጉ አነስተኛ ደረጃ ሙከራዎችም ምንም ዓይነት ከባድ የጎንዮሽ ጉዳት አላሳዩም ነው የተባለው።
ይህ ፈጠራ በተለይም በአደጋ ቀጠናዎች፣ በጦር ሜዳ አካባቢዎች እና ሩቅ በሆኑ ክልሎች የድንገተኛ ጊዜ ደም መስጠትን ለመቀየር ያለመ ነው። ለረጅም ጊዜ የሚቆይ፣ ለአገልግሎት ዝግጁ የሆነ እና ከቫይረስ የጸዳ መፍትሄ በማቅረብ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጃፓን ሁሉንም ክሊኒካዊ ሙከራዎችን አጠናቅቃ ምርቱን በ2030 አካባቢ ወደ ትክክለኛ አገልግሎት ለማዋል ተስፋ ማድረጓ ተመላክቷል።
ምላሽ ይስጡ