ሰኔ 27 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)በቅርቡ በጂኦታብ (Geotab) የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው፣ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባትሪዎች የአፈጻጸም ቅናሽ ሳይታይባቸው እስከ 20 ዓመታት ድረስ ሊቆዩ ይችላሉ። ይህ ደግሞ በአሜሪካ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች አማካይ ዕድሜ ከሆነው 14 ዓመታት እጅግ የላቀ ነው ተብሏል።
ጥናቱ ከ10,000 በላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን መረጃ በመጠቀም የተካሄደ ሲሆን፣ ተመራማሪዎች የባትሪ አቅም በዓመት በ1.8% ብቻ እንደሚቀንስ እና የባትሪ ብልሽት መጠን ደግሞ ከ0.5% በታች መሆኑን አረጋግጠዋል። ይህ ግኝት ስለ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አስተማማኝነት እና ውድ የባትሪ ምትክ ወጪዎች ሲነገሩ የነበሩ አፈ ታሪኮችን የሚያፈርስ ነው ተብሎለታል።
ዝግ ያለ ቻርጅ ማድረግ (Slow charging) እና መካከለኛ የአየር ሙቀት የባትሪውን ዕድሜ ያራዝማሉ። በተጨማሪም፣ እንደ ሊቲየም አይረን ፎስፌት (LFP) ያሉ አዳዲስ የባትሪ ኬሚስትሪዎች ከፍተኛ ጥንካሬ እና የቻርጅ መሙላት ምቹነትን የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የአፈጻጸም ጥራትን ሳይቀንሱ መጠቀም እንደሚቻል ጥናቱ ያመለክታል።
ይህ ጥናት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የረጅም ጊዜ አስተማማኝነትን በተመለከተ ለተጠቃሚዎች እና ለኢንዱስትሪው ትልቅ ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ