ሰኔ 24 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) ባለፈው ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የነበረው አዋጅ ዛሬ ሲጸድቅ ከአዋጁ ስያሜ ጀምሮ ማሻሻያዎች በቋሚ ኮሚቴዎች እንደተደረገ ተገልጿል፡፡
ረቂቁ መፅደቁ ዜጎችን ሊያፈናቅል ይችላል የሚል ስጋታቸውን ያስቀመጡ የምክር ቤት አባላት የከተሞች እድገት ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ሌሎች የሃገሪቱን ክፍሎችንም ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚል ሃሳብ አንስተዋል፡፡
የውጭ ሃገር ባለሃብቶች አሁን ላይ የሚያስፈልጋቸው 150ሺህ ዶላር መሆኑ ተገቢ እንዳልሆነና መጀመሪያ ይዘው መምጣት ያባቸው ገንዘብ ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ የሚናገሩት የምክር ቤቱ አባላት፤ቀድሞ ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መሻሻሉ ጥሩ ሁኖ ሳለ ክልሎችን ተሳታፊ አላደረግም የሚሉ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡
150 ሺህ ዶላር የተደረገው ለመነሻነት እንጂ በሂደት ይጨምራል ሲሉ ከምክር ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የከተማ መሰረተ ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር እሸቱ ተመስገን የማይንቀሳቀስ ንብረት ሲባል በተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ መሰረት አንድ መኖሪያ ቤት እስከ አራት ምኝታ ክፍል ያለው ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የውጭ ሃገር ዜጎች መንግስት የሰራውን ማንኛውንም የመኖሪያ ቤት ከመንግስትም ይሁን በተዘዋዋሪ ከግለሰብ መግዛት እንደማይችሉ ያነሱት ሰብሳቢው፤ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን በሊዝ መሬት የሚያገኙ የውጭ አገር ዜጎች አጠቃላይ የሊዝ ዋጋውን በአንድ ጊዜ የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ለክልሎች ሥልጣን እና ኃላፊነት የሚሰጥ አዲስ አንቀጽ ስለመካተቱም ዶ/ር እሸቱ አብራርተዋል፡፡
የአዋጁ ዋና ትኩረት በመኖሪያ ቤት ብቻ ላይ እንደሆነ ዶ/ር እሸቱ አንስተው ባለሃብቶቹ ከሃገር ውስጥ አልሚዎች መግዛት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የውጭ ሃገር ዜጎች የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚሆኑበት ረቂቅ አዋጅ 1388/2017 በ4 ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ