ሰኔ 24 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ኢንሳ ለትራንስፖርት ምቹ ባለሆኑና በፍጥነት መድረስ የሚገባቸውን እንደ ክትባትና ለግብርና ስራ ጥቅም ላይ የሚዉሉ ኬሚካሎችን በድሮን በመታገዝ እያጓጓዘ መሆኑን ለመናኸሪያ ሬዲዮ አስታውቋል፡፡
ባለፉት ጊዜያት በሲዳማ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን ለክትባት አገልግሎት የሚውሉ መድኃኒቶችን በድሮን በመታገዝ ማድረሱን የተናገሩት በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የፕሮጀክት ሃላፊ አቶ ካሳ ጠና ናቸው፡፡
አሁን ላይ ለኬሚካል ርጭት የሚውሉ ከ50 እስከ 100 ሊትር የሚይዙ ድሮኖች በአስተዳደሩ እንዳሉና በተመሳሳይ መድኃኒትን ለማጓጓዝ አገልግሎት ላይ የሚውሉ እስከ 105 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚጓዝ ድሮን መኖሩን በማመላከት በቅርቡም አገልግሎት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ሀገሪቷ ያላት የቆዳ ስፋት ከፍተኛ በመሆኑ ይህን አካሎ ተደራሽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠትና እንዲሁም ከተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት ምን ታስቧል ያልናቸው ኃላፊው በቀጣይ በስፋት ለመስራትና ከተቋማት ጋር የመቀናጀት እቅድ እንዳላቸዉም ጠቁመዋል፡፡
ምንም እንኳ በስፋት ስራውን ለመስራት አሁን ላይ ያሉ ድሮኖች በቂ ናቸው ባይባልም ፤ በቀጣይ ሀገሪቷ የድሮን ምርትን በሀገር ውስጥ ማምረት በመጀመሯ ለዚህ ዓላማ የሚውሉ ድሮኖች በስፋት ለማሰማራት መታቀዱንም አክለዋል፡፡
በተለይ አሁን ላይ ወቅቱ የክረምት ወቅት እንደመሆኑ መጠን በስፋት ለመስራት ድሮኖችን ለመጠቀም መታቀዱ ተመላክቷል፡፡
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ