ሰኔ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ካናዳ በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ ለመጣል ባቀደችው ታክስ ምክንያት ከካናዳ ጋር ሲካሄድ የነበረውን የንግድ ድርድር ወዲያውኑ ማቋረጣቸውን አስታወቁ።
ትራምፕ ይህን የካናዳ እርምጃ “በሀገራችን ላይ ቀጥተኛ እና ግልጽ ጥቃት” ሲሉ ገልጸውታል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ላይ፣ ካናዳ ሰኞ ዕለት ተግባራዊ ለማድረግ ያቀደችውን የዲጂታል አገልግሎቶች ታክስ (Digital Services Tax) እንደምትቀጥል ለአሜሪካ ማሳወቋን ተከትሎ ይህን ውሳኔ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
ይህ ታክስ በካናዳ ኦንላይን ተጠቃሚዎች ገቢ የሚያስገኙ ካናዳውያን እና የውጭ ኩባንያዎችን ይመለከታል።
ትራምፕ፣ “በዚህ አስከፊ ታክስ ምክንያት፣ ከካናዳ ጋር የምናደርጋቸውን የንግድ ውይይቶች በሙሉ በአስቸኳይ አቁመናል። በሰባት ቀናት ውስጥ ካናዳ ከአሜሪካ ጋር የንግድ ሥራ ለመስራት የምትከፍለውን ታሪፍ እናሳውቃታለን” ብለዋል።
ይህ የትራምፕ ውሳኔ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የጀመሩት የንግድ ጦርነት የቅርብ ጊዜው ምዕራፍ ነው።
ከካናዳ ጋር የነበረው የንግድ ግንኙነት ከዚህ በፊትም በተለያዩ ጉዳዮች ውጣ ውረዶች የነበሩበት ሲሆን፣ በተለይም በብረትና አልሙኒየም ላይ በተጣሉ ታሪፎች ምክንያት ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።
ካናዳ የዲጂታል አገልግሎቶች ታክስ ህግን ባለፈው ዓመት ሰኔ 2024 ያጸደቀች ሲሆን፣ ታክሱ ሰኞ ዕለት ተግባራዊ ለመሆን ቀጠሮ ተይዞለት ነበር። ይህ ታክስ እንደ አማዞን፣ ጎግል፣ ሜታ፣ ኡበር እና ኤርቢኤንቢ ያሉ ኩባንያዎች ከካናዳ ተጠቃሚዎች በሚያገኙት ገቢ ላይ 3 በመቶ የሚደርስ ቀረጥ ይጥላል ነው የተባለው።
የካናዳ የገንዘብ ሚኒስትር ፍራንሷ-ፊሊፕ ሻምፓኝ ባለፈው ሳምንት የዲጂታል ታክሱ ሰፋ ያለ የአሜሪካ-ካናዳ የንግድ ውይይቶች አካል ሆኖ ሊደራደር እንደሚችል ጠቁመው ነበር። ሆኖም፣ የትራምፕ የቅርብ ጊዜ መግለጫ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ወደ አዲስ የውጥረት ደረጃ ያሸጋገረ ሲሆን፣ የንግድ ባለሙያዎችም ይህ ድርድር መቋረጥ በሁለቱም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
ምላሽ ይስጡ