ሰኔ 21 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ) በፓኪስታን ሰሜናዊ ምዕራብ በሚገኘው ሰሜን ዋዚሪስታን ክልል ውስጥ በተፈጸመ ከባድ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት 13 የጸጥታ ኃይሎች ህይወታቸውን ሲያጡ፣ 14 ንፁሃን ዜጎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው የተባለው።
ይህ አደጋ በሰሜን ዋዚሪስታን ከቅርብ ወራት ወዲህ ከተከሰቱት እጅግ ገዳይ ጥቃቶች አንዱ ተብሎ የተገለጸ ሲሆን፣ በክልሉ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩ ተዘግቧል።
የአካባቢው የጸጥታ ምንጮች እንደገለጹት፣ የአጥፍቶ ጠፊው ጥቃት የተፈጸመው ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ላይ ሲሆን፣ ፈንጂ የጫነ ተሽከርካሪ የጸጥታ ኃይሎችን ኢላማ በማድረግ እራሱን በማፈንዳቱ ነው ተብሏል።
በጥቃቱ የተጎዱት ንፁሃን ዜጎች ሴቶችና ህጻናትን ጨምሮ ሲሆን፣ የበርካታዎቹ ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።
ይህ ክስተት በፓኪስታን እና በአፍጋኒስታን ድንበር አካባቢ በሚገኙ የጎሳ ግዛቶች ውስጥ እየተባባሰ የመጣውን የሽብር እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው ተብሎለታል።
የፓኪስታን መንግስት በአካባቢው የጸረ-ሽብር ዘመቻዎችን እያካሄደ ቢሆንም፣ የሽብር ቡድኖች በተደጋጋሚ የጸጥታ ኃይሎችን እና ንፁሃን ዜጎችን ኢላማ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። የሰሜን ዋዚሪስታን ክልል በተለይ ለሽብር ቡድኖች መሸሸጊያ በመሆን ይታወቃል።
የአጥፍቶ ጠፊውን ጥቃት እስካሁን በይፋ የወሰደ አካል ባይኖርም፣ እንደ ተህሪክ-ኢ-ታሊባን ፓኪስታን (TTP) ያሉ ታጣቂ ቡድኖች በአካባቢው ተመሳሳይ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቆይተዋል ነው የተባለው።
ይህ ጥቃት በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢነት ዳግም ያሳየ ሲሆን፣ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ እርምጃዎችን እንዲወስድ ግፊት እየጨመረ ነው ተብሏል።
ምላሽ ይስጡ