👉የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለሥልጣን በበኩሉ የዜጎችን ህገ-መንግስታዊ መብት ያስጠበቀ መመሪያ ነው ብሏል።
ሰኔ 23 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ)ቅሬታቸውን ለመናኸሪያ ሬዲዮ የገለጹት የመዲናዋ ነዋሪዎች ከቤት የሚወጡ ፍሳሾች አወጋገድን በተመለከተ የወጣው መመሪያ ቆሻሻ ለማስወገድ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።
በየመኖሪያ ግቢው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንድናዘጋጅ የሚያስገድደው መመሪያ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ለአቅመ ደካሞች ትልቅ ፈተና ሆኖብናል ሲሉ ገልጸዋል።
ቢያንስ ለመመሪያው ተፈጻሚነት የሚያግዙ ቅድመ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ ፤ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እየገፋን ሳለ፣ ቆሻሻ ውሃ አፍሳችኋል በሚል ቅጣት እየተጣለብን ነው ብለዋል።
በየጊቢያችሁ ጉድጓድ ቆፍሩ ቢባልም ጊቢ የሌለንና ጠባብ ክፍል ውስጥ ለምንኖር አስቸጋሪ እየሆነብን ነው ሲሉ አክለዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ-አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፣ የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት ባስጠበቀ መልኩ እየሰራ መሆኑንና መመሪያውም ንጹህና ደህንነቱ የተጠበቀ አከባቢን ለነዋሪው ለማመቻቸት ያለመ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከቅጣት በፊት ምን ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል ሲል ጣቢያችን ላነሳው ጥያቄ ፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራቱንና ስልጠና እንዲሰጡ ባለሙያዎችን በመመደብ መሠራቱን አክለዋል።
ዋና ስራ-አስኪያጁ መመሪያ ካለው የጤና ፋይዳ አንጻር ትክክለኛ በመሆኑ ቅሬታ የሚያስነሳ አይደለም ሲሉ አመላክተዋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ