ሰኔ 23 ቀን 2017 (መናኸሪያ ሬዲዮ)ቻይና በህዋ ላይ ባደረገችው አስደናቂ ግኝት፣ ከስታርሊንክ (Starlink) በአምስት እጥፍ የሚበልጥ ፈጣን የኢንተርኔት ፍጥነት ማግኘት ችላለች ተብሏል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ከምድር 36,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ አንድ የቻይና ሳተላይት፣ 2 ዋት ብቻ የሚፈጅ ሌዘር በመጠቀም መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በሌዘር ላይ የተመሰረተው ይህ እጅግ ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ፣ የዓለምን የኢንተርኔት ምህዳር የመቀየር አቅም አለው ተብሎለታል። ይህ ቴክኖሎጂ እጅግ ፈጣን እና ዝቅተኛ ኃይል የሚጠቀም የዳታ ስርጭትን በቀጥታ ከህዋ ማድረስ ይችላል ነው የተባለው፡፡
ይህ ግኝት ለወደፊቱ እጅግ በጣም ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ከሳተላይት የማግኘት ዕድልን እንደሚከፍትና 2 ዋት ብቻ መጠቀም መቻሉ የኃይል ፍጆታን በእጅጉ ይቀንሳል፣ ይህም የሳተላይት አሠራርን ይበልጥ ቀልጣፋ ያደርገዋል ተብሎለታል፡፡
ይህ ከዘመናዊው የህዋ ቴክኖሎጂዎች የላቀ እርምጃ ሲሆን፣ በህዋ ላይ ለሚደረጉ የመረጃ ልውውጦች አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍትም ተመላክቷል፡፡
የወደፊቱ የኢንተርኔት ግንኙነት በኬብል (wired) ላይ የተመሰረተ ላይሆን ይችላል፤ ይልቁንም ከምህዋር በሌዘር ጨረሮች የሚተላለፍ ሊሆን ይችላል ነው የተባለው። ይህ ግኝት በዓለም ዙሪያ ለሚኖሩ ሰዎች ፈጣን እና ቀልጣፋ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማድረስ አዲስ ተስፋን ይሰጣል ተብሎለታል።
ቻይና በህዋ ቴክኖሎጂ እና በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ኢንቨስት እያደረገች ሲሆን፣ ይህ አዲስ ግኝትም የዚህ ጥረት አካል ነው። የሌዘር ግንኙነት ከሬዲዮ ሞገዶች ይልቅ በርካታ ጥቅሞች አሉት። ከነዚህም ውስጥ ከፍተኛ የመረጃ ማስተላለፊያ አቅም፣ ዝቅተኛ የኃይል ፍጆታ እና ከጣልቃ ገብነት የመከላከል አቅም ተጠቃሽ ናቸው።
ይህ ቴክኖሎጂ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ከጀመረ፣ በተለይም የፋይበር ኦፕቲክ መሠረተ ልማት በሌለባቸው ሩቅ እና ተደራሽ በሆኑ አካባቢዎች ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሏል። አሁን ያለው የስታርሊንክ ኔትወርክ በሺዎች የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ምህዋር (low-Earth orbit) ሳተላይቶችን በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ የቻይናው አዲስ ቴክኖሎጂ ደግሞ በአነስተኛ ሳተላይቶች ተመሳሳይ ወይም የተሻለ አገልግሎት መስጠት ከቻለ፣ ወጪ ቆጣቢነቱም ይጨምራል ተብሎለታል።
የኢንተርኔት ግንኙነት የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሌዘር የጠፈር ቴክኖሎጂ እጅ ሊሆን እንደሚችል የቻይናው ግኝት ፍንጭ ሰጥቷል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
(https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
የቀጥታ ስርጭት 👉 https://zeno.fm/radio/menahria-99-1-3pw1/ (https://stream.zeno.fm/yw8poig9iwtuv)
Telegram 👉 https://t.me/menaharia_fm
ምላሽ ይስጡ