ሰኔ 18 ቀን 2017(መናኸሪያ ሬዲዮ)የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኔዘርላንድስ ሄግ በተካሄደው የኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ባደረጉበት ወቅት፣ የኔቶን የጋራ መከላከያ አንቀጽ 5 ቁርጠኝነትን በተመለከተ በድጋሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በተጨማሪም አባል ሀገራት ለመከላከያ የሚያወጡትን ወጪ ወደ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 5 በመቶ ከፍ ማድረጋቸውን ማድነቃቸው ተዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከዚህ ቀደም በአንቀጽ 5 ላይ የሰጡት አስተያየቶች የጥቂት የአውሮፓ አጋሮችን ስጋት ቀስቅሰው እንደነበር ይታወሳል። አንቀጽ 5 አንድ የኔቶ አባል ሀገር ጥቃት ሲደርስበት ሁሉም አባላት እንደራሳቸው ጥቃት ቆጥረው በጋራ የመከላከል ግዴታ እንዳለባቸው ይደነግጋል። ፕሬዚዳንቱ ወደ ጉባኤው ሲያቀኑ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ የአንቀጽ 5 ትርጉም “በትርጉምህ ላይ የተመሠረተ ነው” በማለት ለየት ባለ መልኩ ገልጸው ነበር። ይሁን እንጂ፣ ወደ ሄግ ሲደርሱ በሰጡት ይፋዊ መግለጫ፣ ለአሊያንስ ወዳጅነት እና ለሕይወት ደህንነት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል ነው የተባለው፡፡
ትራምፕ ለመከላከያ ወጪ የሚደረገው መዋጮ እንዲጨምር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲከራከሩ መቆየታቸው ይታወቃል። የኔቶ አባል ሀገራት የመከላከያ በጀታቸውን ቢያንስ 2 በመቶ ከፍ እንዲያደርጉ ከዚህ ቀደም የነበረውን ግብ በማንሳት፣ አሁን ደግሞ ወደ 5 በመቶ ከፍ ማለቱን አሞካሽተዋል። “ኔቶ ወድቆ ነበር፣ እናንተ መክፈል አለባችሁ አልኳቸው” ሲሉ፣ የአባላት ሀገራት የመከላከያ ወጪያቸውን እንዲያሳድጉ ባደረጉት ግፊት ስኬት እንዳገኙ ገልጸዋል። አክለውም፣ 5 በመቶው የመከላከያ ወጪ “በጣም ጥሩ ነው” እና “ለአባላት የበለጠ ኃይል ይሰጣል” ማለታቸው ተመላክቷል፡፡
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተም፣ ሁሉም የኔቶ አባል ሀገራት 5 በመቶ የመከላከያ ወጪ ግብ ላይ መስማማታቸውን ለፕሬዚዳንት ትራምፕ በግል መልዕክት ማረጋገጣቸው ታውቋል። ይህ አዲስ የ5 በመቶ ግብ፣ ከቀድሞው 2 በመቶ ግብ በእጅጉ የጨመረ ሲሆን፣ የኔቶ አባላት በጋራ መከላከያቸው ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ተብሎለታል። ሆኖም ይህ የ5 በመቶ ወጪ በሁለት ይከፈላል ተብሏል፤ 3.5 በመቶው ለባህላዊ ወታደራዊ ወጪዎች ሲሆን፣ ቀሪው 1.5 በመቶው ለመከላከያ ተያያዥነት ባላቸው እንደ የመንገድና ድልድይ መሠረተ ልማት ግንባታዎች እና ሳይበር ደህንነት የመሳሰሉ ነገሮች ላይ ሊውል ይችላል ነው የተባለው፡፡
የፕሬዚዳንት ትራምፕ ይህ የመከላከያ ወጪ ጭማሪ የአሜሪካን ትኩረት በኢንዶ-ፓሲፊክ እና በራሷ ድንበሮች ላይ እንዲሆን ያስችላል የሚል እምነት አላቸው። በጉባኤው ላይ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ጋር እንደሚገናኙም ተጠብቋል።
__
ሀሳብ እና’ሳ’ፍራለን
👉011-639-28-52
👉011-639-37-63
ምላሽ ይስጡ